የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ኮምኒኬ መዘየት…

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረ አንድ ሳምንት ቢያስቆጥርም የመጀመርያው የውድድር ኮምኒኬ እስካሁን ለክለቦቹ አልደረሰም።

በ13 ክለቦች መካከል እየተከናወነ የሚገኘው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቃቸው ይታወሳል። ነገ ሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት እንደሚጀመሬም ይጠበቃል። ሆኖም የመጀመርያው ሳምንት እንዳለቀ ለሁሉም ተሳታፊ ክለቦች በኢሜይል መላክ የነበረበት የውጤት፣ የካርዶች፣ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች እና የቀጣይ ሳምንት ውጤቶችን የሚገልፀው የውድድር ኮምኒኬ ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ለክለቦቹ አልተበተነም። የአንድ ሳምንት ውድድር ከተጠናቀ በኃላ ከአንድ ቀን በኃላ ለክለቦቹ ሁሉ መድረስ እንደሚገባው የሚታመነው የውድድር ኮምኒኬ በርከት ያሉ ባለሙያዎች ያዋቀረው የሊግ ካምፓኒው የውድድር ኮሚቴ እስካሁን አለመላኩ አስገራሚ ሆኗል። ለምን መድረስ በሚገባው ጊዜ ሳይደርስ ቀረ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ወደሚመለከታቸው አካላት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ለጊዜው አልተሳካም።

ቢሆንም አስራ ሦስት ክለቦች ብቻ የሚሳተፉበትና እግርኳሱን ለማዘመን በርካት ያሉ ጥረቶች እየተደረጉ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የሊጉ የውድድር ኮሚቴ የጨዋታ ኮሚንኬ በፍጥነት አለማድረሱ በቀጣይ መታረም ያለበት መሆኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ