ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በድሬዳዋ እና ጊዮርጊስ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ድልን ማጣጣም ያልተሳካላቸው ድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ እርስ በእርስ ይገናኛሉ።

ብርቱካናማዎቹ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰበታን በገጠሙበት ጨዋታ ኳስ እና መረብን ሳያገናኙ መውጣታቸው እጅግ አስገራሚ ነበር። ፈጣኑ ጁኒያስ ናንጂቡ ለተከላካዮች እጅግ አደገኛ መሆኑን ባሳየበት ጨዋታ በፈጣን ሽግግር የሚፈጠሩለትን ዕድሎች ይዞ ወደ ሳጥን ውስጥ ደጋግሞ ሲገባ ታይቷል። ተጫዋቹ ይህን ብቃቱን መድገም ከቻለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ጋር የሚኖረው ፍጥጫ ከወዲሁ ተጠባቂ እንዲሆን ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የፊት መስመር ተጫዋቾቹን ጠንካራ ጎን ለመጠቀም በሚረዳው መልኩ የኤልያስ ማሞ በመልካም አቋም ላይ መገኘት ከኋላ መስመሩ የሚቋረጡ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ለማድረስ ረድቶታል። በነገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍ ያለውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሊይዝ መቻሉ እና መሀል ላይ የቁጥር ብልጫን ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል መኖሩ የድሬ የመጀመሪያ ጨዋታ የመልሶ ማጥቃት ጥንካሬ ይበልጥ የሚፈተሽበት ጨዋታ እንዲሆን ያደርገዋል። ከዚህ ውጪ ግን ቡድኑ አሁንም በግብ ፊት ያገኛቸውን ያለቁ ዕድሎች የመጨረስ ችግሩን ካልቀረፈ በድጋሚ ዋጋ መክፈሉ የማይቀር ነው። በዚህ ረገድ ድሬዎች የመስመር አጥቂው አስቻለው ግርማን ዝውውር ማጠናቀቃቸው ሊጠቅማቸው እንደሚችል ሲታመን ኢታሙና ኬይሙኒም ወደ ሜዳ ከተመለሰ የማጥቃት ኃይላቸው ይበልጥ ይጠናከራል።

ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ከሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሦስት ነጥቦች ማግኘት ሳይሳካለት የቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ሁለተኛ ዕድሉን ይሞክራል። ፈረሰኞቹ በፋሲል ከነማ 1-0 በተሸነፉበት ጨዋታ ጥቂት የሚባሉ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም በበቂ ሁኔታ የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል አስጨንቀዋል ማለት ግን አይቻልም። ቡድኑ ለመተግበር እየሞከረ ባለው በኳስ ቁጥጥር እና በአጫጭር ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የመስመር ተከላካዮቹን ሚና ከፍ ለማድረግ እንደሚሞክር ሲታሰብ በአማካይ ክፍሉ ላይም የተጫዋቾች ለውጥ ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል አለ። ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ ከፋሲሉ ጨዋታ ቀነስ ያለ ጫና ሊገጥመው ቢችልም ከግቡ ብዙ ርቆ ላይወጣ የሚችለውን የድሬዳዋን የኋላ ክፍል ሰብሮ ለመግባት የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ከኳስ ዉጪ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ክፍተቶችን ማግኘት ይኖርበታል። በአንፃሩ ባልተሳኩ ቅብብሎች ሳቢያ የሚነጠቁ ኳሶች በፈጣን ሽግግር ለጥቃት ሊያጋልጡት እንደሚችሉ ይገመታል። በዚህ ረገድ ባሳለፍነው ሳምንት ስህተቶችን ሲሰራ የታየው ፓትሪክ ማታሲ እንዲሁም የተከላካይ ክፍሉ ላይ ለውጦች ሊኖሩም ይችላሉ። በተለይም በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በፋሲሉ ጨዋታ በተከላካይ አማካይነት ጨዋታውን ከጀመረው ደስታ ደሙ እና አብዱልከሪም መሀመድ መካከል መምረጥ የአሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ ውሳኔን የሚጠይቅ ይመስላል።

በመጀመሪያው ሳምንት ከሰበታ ጋር በነበረው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና ኩዌኩ አንዶህ በድሬዳዋ በኩል በጉዳት ምክንያት ጨዋታው የሚያልፋቸው ሲሆን ቡድኑ የአንፃሩ ሙኸዲን ሙሳ እና ሄኖክ ኢሳይያስን ግልጋሎት ያገኛል። የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላሀዲን በርጌቾ ፣ አስቻለው ታመነ እና ባህሩ ነጋሽ በተመሳሳይ ለጨዋታው የማይደርሱ ሲሆን ሳላሀዲን ሰዒድ እና የማላዊ ዜግነት ያለው የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ሮቢን ንጋላንዴ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን ሰምተናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ድሬዳዋ ከተማ 3 አሸንፏል፡፡ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጊዮርጊስ 28 ጎሎችን ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 12 ጎሎች አሉት።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)

ፍሬው ጌታሁን

ዘነበ ከበደ – ፍቃዱ ደነቀ – በረከት ሳሙኤል – ሄኖክ ኢሳይያስ

አስጨናቂ ሉቃስ

ሱራፌል ጌታቸው – ኤልያስ ማሞ – እንዳለ ከበደ

ጁኒያስ ናንጂቡ – ኢታሙና ኬይሙኒ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ለዓለም ብርሀኑ

ደስታ ደሙ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

የዓብስራ ተስፋዬ – ሙሉዓለም መስፍን – ከነዓን ማርክነህ

ጋዲሳ መብራቴ – አቤል ያለው – አዲስ ግደይ


© ሶከር ኢትዮጵያ