በሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ መከላከያ ከ ጌዲኦ ዲላ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ2013 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ የመክፈቻ ጨዋታ በሀዋሳ ረፋዱን ጌዲኦ ዲላ ከ መከላከያ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ውድድሩ ጀምሯል፡፡

የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለቱም ዲቪዚዮን ውድድር ዛሬ በሀዋሳ እና አዳማ ተጀምረዋል፡፡ የአንደኛ ዲቪዚዮኑ ውድድሩ ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ ላይ ጌዲኦ ዲላን ከ መከላከያ አገናኝቶ ያለ ምንም ግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ የዓመቱ የመክፈቻ መርሀ ግብር ተከውኗል፡፡ በእለቱ በክብር እንግድነት የፌድሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል እና የሴቶች ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙ እና ሌሎች የፌዴሬሽኑ እንደዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተገኝተው ታድመውበታል፡፡

በርካታ አዳዲስ እና ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች የያዘው መከላከያ እና እንዲሁም በአመዛኙ ጌዲኦ ዲላዎች አብዛኛዎቹን ነባር ተጫዋቾች በመያዝ ጨወታቸውን አከናውነዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጌዲኦ ዲላ ብልጫ በአማዛኙ የታየበት እና የመከላከያዋ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና አስደናቂ አቅም የታየበት ነበረ፡፡ ለዚህም ማሳያ ተከላካዩዋ መንደሪን ክንዲሁን እና አማካዩዋ እፀገነት ግርማ ከቅጣት ምት በሁለት ደቂቃ ልዩነት አከታትለው መተው ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ ያወጣቻቸው ጎሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ወደ ጌዲኦ የግብ ክልል ለመድረስ የታከቱ የሚመስሉት መከላከያዎች ለተጋጣሚያቸው አብዛኛዎቹን የሜዳ ክፍል ለቀው በመጫወታቸው ተጋላጭነታቸውን በይበልጥ አይሎ ታይቷል፡፡

አሁንም መሀል ክፍሉ ላይ ኳስን ለማደራጀት ሲሉ በሰሩት ስህተት በጌዲኦ ዲላ መለያ ደምቃ የታየችሁ እፀገነት ግርማ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ክልል ደርሳ አልቀመስ ያለችሁ ታሪኳ በርገና 28ኛው ደቂቃ ላይ በአስደናቂ ሁኔታ አድናባታለች፡፡ የጨዋታው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው አሁንም ጌዲኦ ዲላ በሰላም ጎሳዬ እና ተከላካዩዋ መንደሪን ክንዲሁን ግልፅ አጋጣሚን ቢያገኙም የታሪኳ በርገና ብልጠት መከላከያዎች ግብ እንዳይቆጠርባቸው ታድጋቸዋለች፡፡
ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠው ካዝገቡ በኃላ ይበልጥ በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸውን ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የመድረስ ዕድላቸውን ያሻሻሉበት ጌዲኦ ዲላ በማጥቃቱ የተዋጣለት ነገር ግን በመከላከሉ ደክሞ የታየበት ክፍለ ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ኤልሻዳይ ግርማን አስወጥተው መሳይ ተመስገንን ካስገቡ በኃላ በመስመር የማጥቃት መንገዳቸውን ወለል ብሎ እንዲከፈትላቸው ቅያሪው አስተዋጽኦ አድርጎላቸዋል፡፡ በዚህም ሂደት ህይወት ረጉ የዲላዎች የመከላከል ድክመት በደንብ ያጠና በሚመስል መልኩ ያገኘቻትን ዕድል ወደ ግብ መታ ግብጠባቂዋ መስከረም መንግስቱ አውጣታለች በተመሳሳይ ተቀይራ የገባችሁ መሳይ ተመስገን ከማህዘን ስታሻማ ፀጋ ንጉሴ በግንባር ገጭታ አሁንም መስከረም ያዳነችባት ሙከራ መከላከያዎች ወደ ጨዋታ ለመመለሳቸው አመላካች አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

ከእነኚህ ሙከራዎች ባሻገር ኤደን ሽፈራው እና ሴናፍ ዋቁማ ከርቀት ጥሩ ጥሩ ሙከራን ማድረግ ቢችሉም የጌዲኦ ግብ ጠባቂ መስከረም ብቂት ጎል ከመሆን ታድጋለች፡፡ በተሰጠው ጭማሪ አራት ደቂቃ ሁለቱ እንደ ተጋመሱ እፀገነት ግርማ ብቻዋን ከታሪኳ ዴቢሶ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝታ ሳትጠቀም የቀረችበት በመጨረሻም ጌዲኦ ዲላዎች ሶስት ነጥብ ለማግኘት ተቃርበው በመጨረሻም ሳይሳካ የቀረበት የማብቂታ ሰአት ግልፅ ሙከራ ብትሆንም ያለ ምንም ግብ ጨዋታው ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ እፀገነት ግርማ የልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ኮከብ ተብላ ተሸልማለች።

ዛሬ ከሰዓት 10:00 ጨዋታው ሲቀጥል አቃቂ ቃሊቲ ከ ድሬዳዋ ከተማ ያገናኛል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ