የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የ2ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መጠናቀቅ ተከትሎ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮችና ዐበይት አስተያየቶች በተከታዩ ፅሁፍ ተዳሷል።


👉 ደፋሩ ካሣዬ አራጌ

በ2ኛው የጨዋታ ሳምንት ብዙ ካነጋገሩ ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ ቡና በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ፋሲል ከነማን 3-1 የረታበት ጨዋታ ነው። በዚህ ጨዋታ ላይ ገና ከሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በአንድ ተጫዋች ከተጋጣሚያቸው ያነሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ለክስተቱ አሰልጣኛቸው ካሣዬ አራጌ የሰጡት ድፍረት የተሞላበት ምላሽ ቡድኑን ውጤታማ አድርጎታል።

አሰልጣኝ ካሣዬ አብዛኞቹ የሀገራችን አሰልጣኞች በመሰል ከባድ ጨዋታ ይቅርና በመደበኛ ጨዋታዎች ላይ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ቢከሰቱ ሊወስኑ ከሚችሉት የተለመደው ጥንቃቄ መር አጨዋወት በተቃራኒ “ፈረስ የጋላቢውን ልብ ያመለከታል” እንዲል ተረቱ የወሰዱት ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ወደ ተጫዋቾቹ ተጋብቶ ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በነበረው ጀብደኝነት ያልተጠበቀ ውጤት አስመዝግቧል።

የተከላካይ ቁጥሩን ለማስተካከል የተከላካይ አማካዩ ዓለምአንተ ካሣን በምንተስኖት ከበደ ከለወጡበት ቅያሬ ውጭ አዎንታዊ ለውጦችን በማድረግ ከፍፁም መከላከል ይልቅ የተወሰደባቸውን የቁጥር ብልጫ በተለዋዋጭ የተጫዋቾች ሚና በማካካስ ብሎም በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው ፋሲል በፍላጎት ልቀው በአዎንታዊ አጨዋወት ሦስት ነጥብ ይዘው ከመውጣታቸው ጀርባ የአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ሚና ከፍተኛ ነበር።

👉 የቡድኖች አቋም ወጥነት ጥያቄ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በጀመረበት ሳምንት ከተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች አራቱ በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ነበሩ። በእነዚህ ጨዋታዎችም ፋሲል ከነማ፣ አዳማ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ ባለ ድል መሆን የቻሉ ቡድኖች ነበሩ። ሆኖም ሁለተኛው ሳምንት ላይ ፋሲል ከነማ ፣ አዳማ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ለሽንፈት ተዳርገዋል። ከሽንፈቱ ባለፈ ቡድኖቹ በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎቻቸው የነበራቸው የጨዋታ ተነሳሽነት እና ልበ ሙሉነት በቀጣዩ ሳምንት ወርዶ ታይቷል። ይህ ሁኔታም ወትሮውንም የወጥነት ችግር የሚንፀባረቅበት ሊጋችን ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው።

በሁለት ሳምንት ጨዋታዎች ሙሉ ለሙሉ መደምደም ቢከብድም አሸናፊ ቡድኖች ቢያንስ ባሸነፉበት ጨዋታ የነበራቸውን ጠንካራ ጎን ለማስቀጠል አሰልጣኞች መጣር እንዳለባቸው መጠቆም ግን ተገቢ ነው።

👉 ሙሉጌታ ምህረት ፈተናውን በሽንፈት ጀምሯል

በኢትዮጵያ እግርኳስ በተለይ በ1990ዎቹ እና በሚሌኒየሙ መጀመሪያ በተጫዋችነት በሀዋሳ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ደማቅ ታሪክን መፃፍ የቻለው ሙሉጌታ ምህረት በ2008 በይፋ ከእግርኳስ ከተገለለ ወዲህ በምክትል አሰልጣኝነት ሚና በሀዋሳ ከተማ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲሰራ ቆይቷል።

ዘንድሮ ደግሞ በተጫዋችነት ዘመኑ ታሪክ የሰራበት ሀዋሳ ከተማ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ በዋና አሰልጣኝነት ተረክቦ የመጀመሪያውን ጨዋታ በዚህ ሳምንት ቢያደርግም በቀድሞ መምህሩ የ3-1 ሽንፈትን በማስተናገድ የዋና አሰልጣኝነት ህይወትን ጀምሯል።

👉 አሸናፊ በቀለ መመለስ

የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በመጀመርያው ሳምንት ቡድናቸው ወላይታ ድቻን ሲረታ በአሰልጣኞች መቀመጫ ሳይሆን ከተመልካቾች ጋር ተቀላቅለው ነበር ጨዋታውን የተከታተሉት። ሆሳዕና ከቀድሞ አሰልጣኙ ኮንትራት ጋር በተያያዘ ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች በመኖራቸው ቡድኑ በምክትሉ ኢያሱ መርሐ ፅድቅ መመራቱ የሚታወስ ሲሆን በትናንቱ ጨዋታ ግን አሰልጣኙ ቡድናቸውን ሲመሩ ተስተውሏል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ባስቆጠረው ጎል ተከታታይ ድላቸውን ላስመዘገቡት ሆሳዕናዎች አሰልጣኝ አሸናፊ የባህር ዳርን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት በሦስት የመሐል ተከላካዮች በመግባት የቀየሱት ዘዴ በመጀመርያው አጋማሽ ውጤታማ የሆነላቸው ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ የቅርፅ ለውጥ እና ውጤታማ ቅያሪዎች በማድረግ ሦስት ነጥብ ይዘው ወግተዋል።

ዐበይት አስተያየቶች

👉 ጳውሎስ ጌታቸው ስለ ወልቂጤው ጨዋታ እና ስለቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ

” በውጤቱ ብዙ አልተከፋሁም። ምንም አይነት የወዳጅነት ጨዋታ ስላላደረግን የዛሬው ጨዋታ ገና ሁለተኛ ጨዋታችን ነው። ከእረፍት በፊት ያገኘናቸውን ሦስት አጋጣሚዎች አስቆጥረን ቢሆን ኖሮ የጨዋታው ውጤት ይቀየር ነበር። የወዳጅነት ጨዋታዎች አለማድረጋችን ወደ ጎል በምናደርጋቸው ሙከራዎች ላይ ይበልጥ ጎድቶናል ፤ ሌሎች ቡድኖች ወደ ውድድር ገብተዋል እኛ ግን ገና ወደ ወዳጅነት ጨዋታ እየገባን ነው።”

👉 ደግአረግ ይግዛው ከጨዋታ ውጭ ስለተባሉባቸው ኳሶች እና ዳኝነቱ…

“በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አልፈልግም ፤ ይህን የሚከታተል የዳኞች ኮሚቴ አለ ስለዚህ የዛሬውን የባለፈውንም ጨዋታውን ተመልክቷል ብዬ አስባለሁ ስለዚህ መመዘን ያለበት ኮሚቴው ነው።”

👉 ካሣዬ አራጌ ቡድኑ ማሻሻል ስለሚገባው ጉዳይ…

“ወደ ፊት ስንሄድ አሁንም ችግሮች አሉ ፤ በሰጪው እና በተቀባዩ መካከል ትክክለኛ የሆነ መግባባት አትመለከትም። ተቀባዩ የሚጠይቅበትና አቀባዩ የሚሰጥበት እንዲሁም አንዳንዴ ሰጪው ባልተጠየቀበት አቀባዩ የሚሰጥበትን ሂደት ትመለከታለህ። ስለዚህም በሚገኙ ክፍተቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን በሰጪው እና ተቀባዩ መሀል ፍፁም መግግባት እንዲኖር መሥራት ይኖርብናል።”

👉 ሥዩም ከበደ በኢትዮጵያ ቡና ስለተሸነፉበት ጨዋታ…

“እስከ እረፍት ድረስ ጥሩ ነበርን በሁለተኛው አጋማሽም በዚያው ልክ እንገባለን የሚል እምነት በሁላችንም ውስጥ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያችን ሜዳ ላይ በተለየ መንገድ ሲቀርብ ለዚያ ምላሽ መስጠት አልቻልንም። የራስ መተማመኑን ለእነሱ በሰጠናቸው ቁጥር የጨዋታ ሚዛኑን እየወሰዱት ሄደዋል። እንደ ቡድን እገሌ በዚህ ደረጃ ነው የሚገኘው ብሎ ለመገምገም ከባድ ነው። የነበረው ነገር ብል እልም የሚል ነገር ነበር። የዛሬው ጨዋታ ለሻምፒዮንነት እንደ መጓዛችን ብዙ ያስተማረን ጨዋታ ነው፤ ስለዚህም ሁላችንም በጋራ ቁጭ ብለን ስተቶቻችንን ለማረም መሥራት ይኖርብናል።”

👉 የፍስሐ ጥዑመልሳን አቤቱታ…

” ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በተሰጠን ሰነድ ሆነ በነበሩ ውይይቶች ከአንድ ክለብ ከ10 በላይ ደጋፊ አይገባም ተብለን ነበር ፤ ዛሬ የሆነው ግን ሌላ ነው እኛ 11ኛ ሰው እንኳን ሳይፈቀድልን በተጋጣሚያችን በኩል ከ50 እስከ 60 የሚሆኑ ደጋፊዎች ገብተው ነበር። ሁለተኛ አቀማመጡም ልክ አልነበረም፤ በኮቪድ 19 ምክንያት ሰው ከሜዳ ቢከለከልም በዚህ ደረጃ ሰዎች ተሰብስበው እንዲጨፍሩ መደረጋቸው አድሎ ነው።ሌላው እኛ ቅጣት ምት ሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝተን ነበር ነገርግን ለእኛ አልተነፋልንም፤ መሰል የዳኞት ከተፅዕኖ ያለመውጣት ነገሮች እስከቀጠሉ እንዴት ነው እግርኳሳሳችንን ማሳደግ የሚቻለው።”

👉 ማሒር ዴቪድስ በተጫዋቾቹ ቅር ስለተሰኙበት ጉዳይ…

“ባሳለፍነው ሳምንት እንደተናገርኩት የትኩረት ማጣት በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ዛሬም ይስተዋል ነበር፤ በዚህም ቅር ተስኝቻለው። ነገርግን ዋናው ሦስት ግቦችን እና ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ቢሆኖም አሁንም የሚቀሩን ብዙ ሥራዎች አሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ