ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ከጨዋታ ብልጫ ጋር አዳማን ረትቷል

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በስንታየሁ መንግሥቱ ሁለት ግቦች አዳማ ከተማን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

አዳማ ከተማ ጅማን ከረታበት ጨዋታ ዘርይሁን ብርሀኑ፣ በላይ አባይነህ እና ፀጋዬ ባልቻን በማሳረፍ ሙጃይድ መሀመድ፣ አክሊሉ ተፈራ እና ፍስሀ ቶማስን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካቷል። በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግዶ የነበረው ወላይታ ድቻ ደግሞ ሰዒድ ሀብታሙ ፣ መሳይ አገኘው ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ኤልያስ አህመድን በመክብብ ደገፉ ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ አብነት ደምሴ እና ነጋሽ ታደሰ ምትክ አሰልፏል።

ወላይታ ድቻዎች እንደመጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ በቶሎ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች መሀል ለመሀል በሰነዘሩት ጥቃት ቸርነት ጉግሳ በግንባር የጨረፈለትን ኳስ የፊት አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። በጨዋታ ረገድም የድቻ የመሀል ተሰላፊዎች የተሻሉ ቅብብሎች በመከወን ቡድኑ አብዛኛውን ደቂቃ በአዳማ ሜዳ ላይ እንዲቆይ አስችለውታል። በተለይም ኤልያስ አህመድ እና እንድሪስ ሰዒድ ለአዳማ አማካዮች አስቸግረው ታይተዋል። ድቻዎች እንደመጀመሪያው ሁሉ በድጋሚ ከአዳማ የተከላካይ ክፍል ጀርባ ያለውን ክፍተት የተጠቀሙበትን ሁለተኛ ግብ 25ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። እንድሪስ ሰዒድ በተከላካዮች መሐል የሳነጠቀለትን ግሩም ኳስ ስንታየሁ በድጋሚ ወደ መረብ ልኳታል።

26ኛው ደቂቃ ላይ ፍሰሀ ቶማስ በቀኝ መስመር ገብቶ ሳጥን ውስጥ ወደ ኋላ ያስቀረለትን ኳስ አክሊሉ ተፈራ ወደ ውጪ ሲልካት የአጋማሹን ብቸኛ አደገኛ ዕድል የፈጠሩት አዳማዎች እጅግ ወርደው ታይተዋል። በተጋጣሚው በእጅጉ የተበለጠው የቡድኑ መሀል ክፍል የግብ ዕድሎችን ለመፍጠርም ሆነ የድቻን አማካዮች ለመቆጣጠር ያልቻለበትን አጋማሽ አሳልፏል። ይልቁንም በድቻዎች በኩል በ36ኛው እና 45ኛው ደቂዋዎች ከእንድሪስ በተነሱ የቅጣት ምት ኳሶች ስንታየሁ እና ቸርነት ተጨማሪ ግቦች ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። የቡድናቸው በጫና ውስጥ መሆን ያሳሰባቸው የአዳማው አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤልም አጋማሹ ሳይጠናቀቅ እዮብ በቀታን በአክሊሉ ቦታ ለውጠው ለማስገባት ተገደዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ትዕግስቱ አበራ ከመሀል ያሻማውን ኳስ እዮብ በቀታ በግንባር ገጭቶ የአዳማን የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም አዳማዎች ልዩነቱን ለማጥበብ ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ ድቻዎች በአንፃሩ ኃይል ለቀላቀለ መከላከልን በመተግበር ድንገተኛ ጥቃት የሚሰነዝሩባቸውን አጋጣሚዎች ይጠባበቁ ነበር። ያም ቢሆን አዳማዎች ከ64ኛው ደቂቃ የታፈሰ ሰረካ የቅጣት ምት ሙከራ በኋላ የመጨረሻ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቆይተዋል። ከዛ ይልቅ 72 ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ደርሰው ቸርነት ጉግሳ ከፀጋዬ ብርሀኑ ተቀብሎ ከርቀት ያረገው ሙከራ አደገኛ ነበር።

በሂደት ከኃይል አጨዋወቱ እየወጡ ኳስ ወደ መያዙ የመጡት ድቻዎች እንድሪስ እና ቸርነትን በመቀየር ፀጋዬ ባልቻ እና ነጋሽ ታደሰን በማስገባት በአዲስ ኃይል ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመውጣት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። በአንፃሩ አብዲሳ ጀማል እና ፀጋዬ ባልቻን አስገብተው የማጥቃት ኃይላቸውን ለማጠናከር የሞከሩት አዳማዎች ያሰቡትን ብልጫ ማሳካት እና የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ስንታየሁ እና ነጋሽ አማካይነት የረጅም ርቀት ሙከራዎችን ያደረጉት ድቻዎች እጅግ በተረጋጉ ቅብብሎች በመከወን ጨዋታውን ያለጫና ተቆጣጥረው ለመጨረስ ችለዋል።

በጨዋታው የመጠናቀቂያ ደቂቃ አስቀድሞ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቶ የነበረው የድቻው አናጋው ባደግ በሁለተማ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ