ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የነገ ረፋዱን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

እንደ አዳማ ከተማ ሊጉን ቁለል ብሎ የጀመረ ክለብ ያለ አይመስልም። ከሜዳ ውጪ በነበረበት ችግር ሙሉ ስብስቡን መጠቀም ያልቻለውን እና በጨዋታውም ተጫዋች በቀይ የወጣበትን ጅማ አባ ጅፋርን በሰፊ ጎል ለማሸነፍ እምብዛም አልተቸገረም ነበር። ነገ ደግሞ በመጀመሪያው ጨዋታ የተሸነፈውን እና ከሽንፈት ለማገገም የሚጥረው ድቻን ይገጥማል። በጨዋታውም አዳማ በእርግጥም ጠንካራ ቡድን መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል። አዳማ በመጀመሪያ ጨዋታው የተዋጣለት የመስመር ተከላካዮች አጠቃቀም፣ የተረጋጋ የተከላካይ አማካዮች ጥምረት እና ጥሩ የአጨራረስ ብቃትን አሳይቶን አልፏል። ሆኖም አልፎ አልፎ በጅማ ተጫዋቾች ይወሰድበት የነበረው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማፈግፈግ ሲያስገድደው ይታይ ነበር። ይህ ሲታሰብ ቡድኑ ከበድ ባለ ጫና ውስጥ ጨዋታዎችን ሲያደርግ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለውን ጥያቄ ነገ እንድንመለከት የሚያደርገን ነው። ከዚህ ውጪ ግን የመጀመሪያውን ጨዋታ በቀላሉ ድል ማድረጉ ለነገው ግጥሚያ በተጫዋቾች ላይ የሚፈጥረው የስነ ልቦና ጥንካሬ የማይካድ ነው። በቀላል ስህተት የተቆጠረበት ግብን ግን እንደማንቂያ ደውል ሊያየው ይገባል።

ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በመጀመሪያው ጨዋታ ከመምራት ተነስቶ ለሽንፈት መዳረጉ በስብስቡ ላይ አዕምሯዊ ጫና እንዳያደርስበት ያሰጋዋል። ከሽንፈቱ ባሻገር ቡድኑ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጨዋታውን በጀመረመበት ንቃት መቀጠል አለመቻሉ ተቀርፎ ሊመጣ የሚገባው ደካማ ጎኑ ሆኖ ታይቷል። እንደ ቸርነት ጉግሳ ያሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች በሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በወጥ ብቃት የመጫወት ግዴታም ይኖርባቸዋል። ድቻ ከኳስ ውጪ በቆየ ቁጥር የመቸገሩን ያህል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተለይም ኤልያስ አህመድ እና በረከት ወንድሙ ተቀይረው ከገቡ በኋላ በፈጣን ሽግግር ወደ ጎል የመድረስ ጥንካሬ እንዳለው የሀዲያው ጨዋታ አሳይቶናል። ከዚህ ባለፈ ከበረከት ወልዴ በቀጣታ ተጥሎ በቸርነት ድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት የተቆጠረው ኳስም እንዲሁ ወላይታ ድቻ በመልሶ ማጥቃቱ ረገድ ያለውን አስፈሪነት የሚያሳይ ነው። በመሆኑም በነገው ጨዋታ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች በሚኖርባቸው አጋጣሚዎች የድቻ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የአዳማ የተከላካይ ክፍል ጋር የሚኖራቸው ትንቅንቅ ተጠባቂ ይሆናል።

በጨዋታው አዳማ ከተማ ሱሌይማን መሀመድን በጉዳት የማይጠቀም ሲሆን ተቀይሮ በመግባት ጅማ ላይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አብዲሳ ጀማልም ቀለል ያለ ጉዳት እንደገጠመው ተነግሯል። ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ፍኒያንስ ተመስገን ፣ ያሬድ ዳንሳ እና እዮብ ዓለማየሁ ደግሞ በወላይታ ድቻ በኩል በጉዳት ከጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 10 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ድቻ 4 አሸንፏል። በቀሪዋ አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በአስሩ ጨዋታዎች 22 ጊዜ ኳስ እና መረብ ሲገናኙ ሁለቱም እኩል 11 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ታሪክ ጌትነት

ታፈሰ ሰርካ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቴዎስ

ዘሪሁን ብርሀኑ – ደሳለኝ ደባሽ

ፀጋዬ ባልቻ – በቃሉ ገነነ – ፍሰሀ ቶማስ

የኋላእሸት ፍቃዱ

ወላይታ ድቻ (4-2-3-1)

መክብብ ደገፉ

አናጋው ባደግ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ – አብነት ደምሴ

ነጋሽ ታደሰ – ኤልያስ አህመድ – ቸርነት ጉግሳ

ስንታየሁ መንግሥቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ