የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት አካል የሆነ ጨዋታ ዛሬ ተካሂዶ ወላይታ ድቻ ቦዲቲ ላይ አዳማ ከተማን አስተናግዶ ድል አድርጓል፡፡ ተከታታይ ድል በማስመዝገብም ደረጃውን አሻሽሏል፡፡
የወላይታ ድቻ 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ የወላይታ ድቻ ግቦች የተገኘሁት በመሳይ አንጪሶ እና ዮሴፍ ዴንጌቶ አማካኝነት ነው፡፡ መሳይ በ24ኛው ደቂቃ በግምት ከ20 ሜትር ርቀት በግሩም ሁኔታ ቀዳሚዋን ግብ ሲያስቆጥር ዮሴፍ ዴንጌቶ 85ኛው ደቂቃ ላይ 2ኛውን ግብ አክሏል፡፡
ቀይ ካርዶች እና ቅሬታዎች
የመጀመርያውን ግብ ከመረብ ያሳረፈው መሳይ በ63ኛው ደቂቃ በ2ኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ድቻዎች የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ክስ አስመዝግበዋል፡፡ የመሳይ የመጀመርያ ቢጫ የተገኘው ግብ አስቆጥሮ ማልያውን በማውለቅ ደስታውን በመግለፁ ሲሆን ሁለተኛው ቢጫ ደግሞ የማእዘን ምት በሚሻማበት ወቅት በሰራው ጥፋት ነው፡፡ ከ10 ደቂቃዎች በኋላ የአዳማ ከተማው ሚካኤል ጆርጅ በዮሴፍ ዴንጌቶ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡
በጨዋታው ቅሬታ የተሰተናገደበት ሌላው ክስተት በመጀመርያ የተመደቡት ኢንተርናሽናል አርቢቴር አማኑኤል ሃይለስላሴ የአፍሪካ የክለቦች ውድድርን ለመዳኘት ከሃገር ውጪ በመሆናቸው በፌዴራል ዳኛ ተፈሪ መተካታቸው ነው፡፡ አዳማ ከተማ ድንገተኛ የዳኛ ምደባው አግባብ አይደለም በሚል ቅሬታ አቅርቧል፡፡
በድሉ መርዕድ . . .
በድሉ ለዛሬው የድቻ ድል አስተዋፅኦ ካደረጉ ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴን ሲመራ የነበረው በድሉ በክህሎቱም በተመልካቹ ሙገሳ ተችሮታል፡፡
የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች. . .
የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ለቡድኑ ድል ወሳኙን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በስታድየሙ ከተገኙ ተመልካቾች አመዛኞቹ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ሲሆኑ ተማሪዎችም የትምህርት ቤት መለያ ልብሳቸውን እንደለበሱ ስታድየም በመገኘት ክለባቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዥ
አዳማ ከተማ ሽንፈቱን ተከትሎ 23 ነጥብ ላይ በመርጋት የሊጉን መሪነት የመያዝ እድሉን አበላሽቷል፡፡ ወላይታ ድቻ ደግሞ ወደነበረበት 6ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
የጨዋታውን ዋና ዋና ሁነቶች ይህንን ሊንክ በመከተል ማንበብ ይችላሉ፡- http://soccerethiopia.net/?p=6168