በወላይታ ድቻን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በቡድኑ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ካለው እንድሪስ ሰዒድ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ለፕሪምየር ሊጉ ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ቆይታ አድርጓል። ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሊግ የተለያዩ ክለቦች ተጫውቷል። ለወላይታ ድቻ በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ቡድኑ በመሐል ሜዳው ላይ ኳሱን ተቆጣጥሮ እንዲጫወት እና በተቃራኒ ቡድን ላይ ብልጫ እንዲወስዱ በማድረግ የእንድሪስ ሚና የላቀ ነው። በ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታው ሲደርስ ወላይታ ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ እንድሪስ በተለይ ከኤልያስ አህመድ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ለአዳማ ተጫዋቾች ምን ያህል ፈታኝ እንደነበረ በዛሬው ጨዋታ ላይ መታዘብ ችለናል። ይልቁንም ስንታየሁ መንግስቱ ላስቆጠራት ሁለተኛ ጎል እንድሪስ ሰዒድ በተከላካዮች መሐል የሰነጠቀለትን ግሩም ኳስ ተጫዋቹ በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው። ይህን ተከትሎም ከዛሬው ጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ እንድሪስ ሰዒድን አግኝተነው በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ አጠር ያለ ቆይታን አድርጓል።
“በፕሪምየር ሊግ መጫወት ከጀመርኩ አሁን ሁለተኛ ዓመቴ ነው። እንደ መጀመርያ ዓምና የነበረኝ ቆይታ ብዙ ልምድ ያገኘሁበት ነው። ዘንድሮም ከዓምናው የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እሞክራለሁ። ባለፈው ከሀድያ ጋር በነበረው ጨዋታ ይዘነው የገባነውን አጨዋወት ማስቀጠል ባለመቻላችን ውጤቱን ማስጠበቅ ሳንችል ቀርተናል። ይህን ስህተታችንን ተነጋግረን በልምምድም ላይ አርመን በዛሬው ጨዋታ ላይ እስከ መጨረሻው ድረስ ወጥ በሆነ አጨዋወት ለመቅረብ አስበን ወደ ሜዳ የገባነው ጥሩ ሆነን ወጥተናል። ሜዳው ውስጥ የማስበውን ነው የማደርገው። ኳሱን መቆጣጠር አለብኝ ለቡድን አጋሮቼ በተለይ ለአጥቂዎች በቂ የጎል እድል የሚፈጥሩበትን ኳሶች አመቻችቼ ማቀበል ይገባኛል። ያንነው ሜዳ ውስጥ የማደርገው። ኳሱን አብዝቼ ሜዳ ውስጥ በተቆጣጠርኩ ቁጥር ግጭት ያጋጥመኛል ብዬ አልፈራም። ግን በእንቅስቃሴዬ ራሴን ነፃ እያደረኩ ለመጫወት ሞመከሬ ጠቅሞኛል። በቀጣይ አሁን ያለኝን ጥሩ ነገር ለማስቀጠል የቻልኩትን ነገር አደርጋለው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ