ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንትን የተመለከቱ ዐበይት ጉዳዮችን የተመለከትንበት አራተኛ ክፍል ዕነሆ! 

👉አሳሳቢው የመገናኛ ብዙሃን አባላት እንግልት

የዘንድሮው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀደምት ዓመታት በተለየ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በማግኘቱ ለስፖርት ቤተሰቡም ሆነ ለመገናኛ ብዙሃን አባላት የተሻለን አማራጭ እየፈጠረ ይገኛል።

ከስርጭቱ ባሻገር ቁጥራቸው ጥቂት የሚባሉ የመገናኛ ብዙሃን አባላትን ጨዋታዎችን ለመታደም ወደ ስታዲየም ማምራታቸው አልቀረም። ሆኖም እነዚሁ አባላት ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ለመግባት ብሎም ከተገባ ወዲህ መቀመጫ ለማግኘት የሚያልፉት ውጣ ውረድ ግን እጅግ አድካሚ ብሎም “ስለምን ወደ ስታዲየም መጣሁ?” የሚያስብሉ መሆናቸውን ባለፉት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት መታዘብ ችለናል።

ዓአለም አቀፉ ወረርሽኝ መከሰት ጋር በተያያዘ ወደ ስታዲየም የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር መመጠን አስፈላጊ ስለሆነና ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ በመግቢያ በሮች ላይ ያለውን አጠቃላይ ሂደት በበላይነት የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲከውኑ መድረጉ ይስተዋላል ። ይህ ከደህንነት መመዘኛዎች አንፃር ጥሩ የሚባል ቢሆኑም በአንዳንድ መለኪያዎች ዘንድ ግን ክፍተቶች ይስተዋልበታል።

በተለይ ለአዲሱ የውድድር ዘመን የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙሃኖች የመግቢያ ካርድ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ባር ኮድ ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል። ታድያ በዚህ ኮድ ላይ የድርጅቱ ስም እና ወደ ስታዲየም እንዲገቡ እውቅና የሰጣቸው ባለሙያዎች በዝርዝር የተቀመጡበት ሁኔታ እያለ በመግቢያ በሮች የተመደቡት የፖሊስ አባላት ቴክኖሎጂው በተመለከተ ተግባቦት ስልጠና ባለሰተሰጠበት እንዲሁም ማንበቢያ መሳሪያዎች (መተግበርያ የተጫነበት ስልኮች) ባልተሟላበት ሁኔታ ይህን መታወቂያ ተጠቅሞ በፖሊስ አባላት ከሚጠበቀው በር ለማለፍ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን መውሰዱ የተለመደ ነው ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከጨዋታ ጨዋታ የፖሊስ አባላት መቀያየራቸውን ተከትሎ ይህ ሂደት በቀን ሁለት ጊዜ በጨዋታ ሳምንት ደግሞ በሦስት የተለያዩ ቀናት መደጋገሞ ምን ያህል አድካሚ ብሎም አታካች እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

ይህ ሒደት ታልፎ ወደ ሜዳ ከተገባም ወዲህ እንግልቱ ይቀጥላል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ የተፈቀደላቸው ስፍራ የቀኝ/የግራ/ ጥላፎቅ እንደሆነ ቢነገርም ወደ ስፍራ እንዳይገቡ በፖሊስ አባላት ሲከለከሉ ብሎም ሲዋከቡ ይስተዋላል። ከብዙ ሂደት በኃላ ቢገቡም ስፍራውን ከተጋጣሚ ቡድኖች ተጠባባቂ ተጫዋቾች ጋር የሚጋሩት ከመሆኑ አንፃር የወቅቱን የኮቪድ ፕሮቶኮል በተጠበቀ መልኩ ከተጫዋቾቹ በራቀ ሁኔታ እንዳይቀመጡም በስታዲየሙ በተጠቀሱት ክፍል የሚገኙ ወንበሮች በመነቃቀላቸው የተነሳ ባለሙያዎቹ ለከፍተኛ እንግልት እየታደረጉ ያገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ በተቋማት ብሎም አክሲዮን ማህበሩ ያዘጋጃቸው የተለያዩ መግቢያዎችን በማመሳሰል በርከት ያሉ ከተቋማቱም ሆነ ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጭ የተሰሩ መግቢያ ካርዶች በጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛል ፤ ታድያ በተመሳሳይ ይህን አካሄድ ከወዲሁ ስር ሳይሰድ አክሲዮን ማህበሩ ሀሰተኞቹን ከይፋዊዎቹ የመለየት ስራ በአፋጣኝ መስራት ይጠበቅበታል።

👉የፌደሬሽኑ አመራሮች ስለምን ከስታዲየም ራቁ?

ካለፈው አመት ወዲህ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ራሱን ችሎ በተሳታፊ ክለቦች በተዋቀረ የአክስዮን ማህበር እየተመራ መሆኑ ይታወሳል። የሊጉን አስተዳዳሪነት ለአክሲዮን ማህበሩ ያስረከበው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላት ሆነ ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎችም አምና በስታዲየሞች በመገኘት ጨዋታዎችን ሲመለከቱ ይስተዋል ነበር።

ከተጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለወትሮው ለስታዲየሙ ቅርብ የነበሩ የፌደሬሽኑ ሰዎች አሁን ላይ ግን በስታዲየም ሲታደሙ አይስተዋልም። በጉዳዩ ዙርያ ባደረግነው መጠነኛ ማጣራት በምክንያትነት እየቀረበ የሚገኘው በፌደሬሽኑ አመራሮች እና በአክስዮን ማህበሩ ሰዎች መካከል ቅራኔዎች ሳይኖሩ እንዳልቀረ እየተነገረ ይገኛል።

👉ትኩረትን የሚሻው የዳኞቻችን ጉዳይ

የእግርኳስ ዳኝነት እና ስህተት የሚነጣጠሉ ነገሮች ባይሆንም በተቻለ መጠን ግን ስህተቶችን ለመቀነስ የዳኝነት ሒደቱ በተለያዩ ዓለማት በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ እየተደረገ ይገኛል።

አዲሱ የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቴሌቪዥን መተላለፉን ተከትሎ ለወትሮውም ቢሆን በስህተቶች የተሞላ ስለመሆኑ ከፍተኛ ትችት የሚቀርብበት የሀገራችን የእግርኳስ ዳኝነት ከአዲሱ የዳግም ምልሰት እና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት ቀርበው ህዝቡ ፍርድ ሊሰጥባቸው ከሚችለው አዲሱ ዘመን ጋር ዳኞቻችን እንዴት እንደሚጓዙ መመልከት እጓጊ የነበረ ክስተት ነበር።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ከጅማ አባጅፋር ጋር አቻ ሲለያዩ ረዳት ዳኛ አንድነት ዳኜ በአራት አጋጣሚዎች ከጨዋታ ውጭ ያልነበሩ የኳስ እንቅስቃሴዎችን ከጨዋታ ውጭ በሚል ስለማቋረጡ የሱፐር ስፖርት ምስሎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ዳኛው ከእነዚህ አጋጣሚዎች በተጨማሪ በጥቅሉ ከጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር የነበሩት አንፃራዊ አቋቋሞችም በበርካታ ስህተቶች የተሞሉ ነበሩ ። መሰል የቴክኖሎጂ ድጋፍ የማይሹ መሠረታዊ የዳኝነት ብቃት መለኪያ የሆኑ መመዘዎች ከወዲሁ ጎልህ ክፍተቶች መታየት መጀመራቸው
በአጠቃላይ በሊጉ ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንምና የሚመለከተው አካል መላ ሊላቸው ይገባል።

👉የስታዲየም ማስታወቂያዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ከቴሌቪዥን ስርጭቱ ጎን ለጎን ጨዋታው በሚከናወንበት የአዲስ አበባ ስታዲየም መጫወቻ ሜዳው ዙርያ የማስታወቂያ ቦርዶችን መመልከት ብዙም የተለመደ ባይሆንም በአዲሱ የውድድር ዘመን ግን ከወትሮው በተለየ የሜዳው ዙርያ በማስታወቂያ ቦርዶች ጠቅጠቅ ብለው እየተመለከትን እንገኛለን።

የውድድሩን የስርጭት መብት ከገዛው ኩባንያ ዲኤስቲቪ እና የውድድር የስያሜ መብት ባለቤት ቤትኪንግ አወራራጅ ድርጅት በተጨማሪ እንደ ተጋጣሚ ክለቦቹ የሚቀያየሩ የክለቦቹ ስፖንሰር ተቋማት ማስታወቂያ ያዘሉ ቦርዶችን መመልከት መጀመራችን ገቢ ለማመንጨት ይቸገር ለነበረው እግርኳሳችን ተስፋ ሰጪ ጅምር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል።

👉የኮቪድ ፕሮቶኮል እና የዳዋ ቀይ ካርድ

በዚህ የጨዋታ ሳምንት በትናንትናዋ የሀዳያ ሆሳዕናና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ የሳምንቱ ሁለተኛ ቀይ ካርድ ተመዝግቧል። ካርዱን የተመለከተው ዳዋ ሆቴሳ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ወደ ደጋፊዎች በመሄድ በመግለፁ ነበር። የሊጉ ጨዋታዎች በኮቩድ ፕሮቶኮል መሰረት እየተካሄዱ እንደሆነ ይታወቃል። በቁጥር ጥቂት ሆነው በሚገቡ ደጋፊዎች እና ጋዜጠኞች አቀማመጥ ላይ የሚታየው ርቀትን ያለመጠበቅ ጉዳይ ችላ የተባለ ይመስላል። መዘናጋቱ ወደ ሜዳ ውስጥ ዘልቆም ዳዋ ከደጋፊዎች ጋር ንክኪ በመፍጠሩ የሁለተኛ ቢጫ ካርድ ሰለባ እንዲሆን አድርጎታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ