የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ትኩረትን የሳቡ ተጫዋች ነክ ጉዳዮች በቀጣዩ ፅሁፍ ተዳሰዋል።

👉ከግብ የተራራቁት የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች

አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ሁለተኛ ሳምንቱ ላይ ደርሷል። በዚህም እስካሁን በተደረጉ 12 ጨዋታዎች በድምሩ 32 ግቦች ሲቆጠሩ እስካሁን በግብ አግቢነት የተመዘገበ አንድም የውጭ ሀገር ተጫዋች አለመኖሩ አስገራሚ ሆኗል።

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሊጉ ተሳታፊ በነበሩ ክለቦች ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በተለይም አጥቂና ግብ ጠባቂዎች ማግኘት የተለመደ ከመሆኑ መነሻነት በቁጥር በርከት ያሉ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በየጨዋታ ሳምንታቱ ለየክለቦቻቸው በግብ አስቆጣሪነት ሆነ በሌሎች መመዘኛዎች ተፅዕኗቸው ከፍ ያለ ነበር። የፕሪምየር ሊጉ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ በርከት ያሉ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች መመልከት የተለመደ ነበር። ነገርግን ካለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ወዲህ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በግቦች ላይ ያላቸው ተሳትፎ (በማስቆጠርም ሆነ በማመቻቸት) በአንፃራዊነት እየቀነሰ መጥቷል።

ለማሳያነትም በ2ኛ ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ሶስት (ቢስማርክ አፒያ ፣ ሮቢን ንጋላንዴ እና ጁንያስ ናንጂቡ) ብቻ በቋሚነት የጀመሩ የውጭ ሀገር የአጥቂ ተጫዋቾች ሲሆኑ በጥቅሉ ከቁጥራቸው መቀነስ ጋር በተያያዘ እስካሁን ግብ ማስቆጠር አለመቻላቸው በሊጋችን እያነሰ የመጣውን የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ተፅዕኖ በማሳያነት ሊቀርብ ይችላል።

👉ሱራፌል ዳኛቸውን ያያችሁ?

ባለፉት ሁለት ዓመታት በፋሲል ከተማ እጅጉን ከጎለበቱ እና ከደመቁ ተጫዋቾች በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ከክለብም አልፎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀዳሚ ተመራጭ እስከመሆን ያበቁትን አስደናቂ ጊዜያትን አሳልፏል።

ዘንድሮ ግን ያ ባለፉት ዓመታትን የምናውቀው አልሸነፍ ባዩ ፣ ሜዳ ላይ ያለውን የሚሰጠው ፣ ከምንም ተዐምርን መፍጠር የሚችለውን ተጫዋቾች ሜዳ ላይ እየተመለከትን አንገኝም። እርግጥ ነው የትኛውም ተጫዋች በእግርኳስ ህይወቱ መሰል ዝቅታዎችን ማስተናገዱ የማይቀር ቢሆንም በእንደ ሱራፌል ዳኛቸው ደረጃ ደጋፊ ሁሌም ሜዳ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ የሚጠብቃቸው ተጫዋቾች ሁሌም ቢሆን ከፍ ባለ የብቃት ደረጃ ቡድናቸውን እንዲያገለግሉ ይጠበቃል።

የፋሲል ከነማ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው በዚህ ደረጃ መዳከም እንደአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍ ያለ ከመሆኑ አንፃር ተጫዋቹ በአፋጣኝ ነገሮችን በማስተካከል ወደቀደመው ብቃቱ ለመመለስ መስራት ይኖርበታል። ተጫዋቹ ከጉዳት ጋር እየታገለ የውድድር ዓመቱን እንደመጀመሩ አቋሙን ለማስተካከል እረፍት ማድረግም እንደ አማራጭ የሚታይ ነው።

👉በናፈቀው ሜዳ ብዙም መቆየት ያልቻለው ተመስገን ካስትሮ

በ2010 የክረምቱ የዝውውር መስኮት አርባምንጭ ከተማን ለቆ ኢትዮጵያ ቡናን በተቀላቀለ በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር የቡናማዎቹን ደጋፊዎች ልብ መግዛት የቻለው። በ2011 የውድድር ዘመን ጥር 19 ኢትዮጵያ ቡና በጅማ አባጅፋር በተሸነፈበት ጨዋታ ባጋጠመው አሰቃቂ ጉዳት ላለፉት ሁለት ዓመታት ለተጠጉ ጊዜያት በኢትዮጵያ ቡና የነጥብ ጨዋታን ማድረግ ሳይችል ቀርቷል።

ዓምና በተሰረዘው የውድድር ዘመን ከ10ኛው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና የቡድን ስብስብ ውስጥ ቢካተትም ጨዋታዎችን ማድረግ ሳይችል ቀርቷል። በ2ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግን የወንድሜነህ ደረጀ በጉዳት አለመኖርን ተከትሎ ፋሲል ከተማን በገጠመው የኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ 11 ውስጥ በመካተት ጨዋታ ማድረግ ችሏል።

ነገርግን ለረጅም ጊዜያት ሲናፈቅበት በነበረው ሜዳ ላይ ግን መቆየት የቻለው ለ46 ያክል ደቂቃዎች ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአደገኛ ቀጠና የተነጠቁትን ኳስ ተጠቅሞ ሙጂብ ቃሲም ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ሲገሰግስ ተመስገን ካስትሮ ለቡድኑ መስዋዕት በመሆን ተጫዋቹ ላይ ጥፋት በመሥራቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

በቀይ ካርድ ከሜዳ በሚወጣበት ወቅትም ስሜቱ እጅጉን ተነክቶ ሲያለቅስ የተስተዋለበት ክስተት እጅግ ልብን የሚነካ ነበር።

👉የወረደው ፓትሪክ ማታሲ

የሀራምቤ ኮከቦቹ ተቀዳሚ የግብ ዘብ የሆነው ፓትሪክ ማታሲ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ የውድድር ዘመኑ ላይ ይገኛል። የዘንድሮው የውድድር ዘመን አጀማመሩ ግን እንደቀሙት ሁለት ዓመታት ጥሩ አልሆነለትም።

በመጀመሪያ ሳምንት በፋሲል ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ የጨዋታውን ውጤት የወሰነ ይቅር የማይባል ስህተት የፈፀመው ተጫዋቹ በዓርቡ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ምንም እንኳን ቡድኑ ድል ያድርግ እንጂ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ አልፎ አልፎም ቢሆን ከድሬዳዋ ተጫዋቾች የተደረጉበትን ሙከራዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ለማዳን ሲቸገር ተስተውሏል። በተለይም በ58ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታበት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ የጁኒያስ ናንጂቡ ሙከራዎች የግብ ጠባቂውን ወቅታዊ ብቃትን ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ናቸው።

👉መጥፎ ቀን ያሳለፈው ዘነበ ከበደ

በድሬዳዋ ከተማ ከተፈጥሮአዊ ቦታው ውጭ ቡድኑ ካለበት የተጫዋቾች እጥረት የተነሳ በግራ መስመር ተከላካይነት እየተጫወተ የሚገኘው ዘነበ ከበደ በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 የተሸነፉበት ጨዋታን መልሶ ማስታወስ የሚፈልግ አይመስልም።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን መንፈስ የቀየሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኟቸው ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች እሱ በፈፀማቸው ጥፋቶች የተገኙ መሆናቸው ሲታሰብ ተጫዋቹ በተጫዋችነት ዘመኑ ካሳለፋቸው መጥፎ ቀናቶች አንዱ እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም።

👉ከተጠባባቂነት በመነሳት ጨዋታዎችን እየወሰነ የሚገኘው ዱላ ሙላቱ

ከአዳማ ከተማ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ካመሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ዱላ ሙላቱ ነው። ቡድኑ ባሸነፈባቸው ሁለት ጨዋታዎችም ዱላ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ወሳኝ ሚናዎችን ተወጥቷል። በወላይታ ድቻው ጨዋታ ከዳዋ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን አሸናፊ ሲያደርግ በዚህ ሳምንትም ዳግም ተቀይሮ ገብቶ ብቸኛዋን የዳውን ጎል አመቻችቶ አቀብሏል። ፈጣኑ ዱላ ይህ ተፅዕኖው ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል ወይስ ‘ጨዋታ ቀያሪ ተጠባባቂ’ የሚል ቅፅል አሰጥቶት በተጠባባቂነቱ ይቀጥላል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል።

👉በአዲስ ሚና ብቅ ያለው ቢያድግልኝ ኤልያስ

በ2005 የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስብስብ አካል የነበረው እና በወቅቱ ከነበሩ የመሀል ተከላካዮች እጅግ ከፍ ባለ የራስ መተማመን እንዲሁም ከኳስ ጋር ካላው ምቾት አንፃር የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችሎ ነበር።

ሲዳማ ቡናን ለቆ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ ወዲህ ግን እድገቱ በሚጠበቀው ደረጃ አልሆነም። ይልቁኑ ሳይጠበቅ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት በአመዛኙ ከተጫወተባቸው ደቂቃዎች የሚልቀውን በተቀያሪ ወንበር ለመቀመጥ ተገዶ ተስተውሏል። ዘንድሮ ግን በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሰበታ ከተማ ግን ዳግም ፀሐይ የወጣችለት ይመስላል።

በመጀመሪያው ሳምንት ከመሳይ ጳውሎስ ጋር በመሐል ተከላካይ ስፍራ የተሰለፈው ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከተለመደበት የተከላካይ ስፍራ በተለየ በተከላካይ አማካይነት ሚና ጨዋታን ማከናወን ችሏል።

👉እያደገ የመጣው ፉአድ ፈረጃ

ዓምና በአዳማ ከተማ በቂ የመሰለፍ እድልን አያግኝ እንጂ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ድንቅ አማካይ ስለመሆኑ ፍንጮችን ያሳይ የነበረው ፉአድ አሁን ላይ ግን ዕድገቱ በግልፅ እየታየ መጥቷል። በዚህ ሳምንት ሰበታ ከተማ ሀዋሳን ሲረታ ግብ ማስቆጠሩ ብቻ ሳይሆን በጨዋታው ላይ የነበረው ተፅዕኖ በግልፅ የሚታይ ነበር። የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን በሚያሳይ መልኩ እሱ የተሰለፈበት የቀኝ መስመር የሰበታ ጠንካራው ጎን ሆኖ ታይቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከኳስ ጋር በሚገናኝባቸው ቅፅበቶች ተጫዋቾችን ለመጋፈጥ የነበረው ድፍረት እና ወደ መሀልኛው የሜዳ ክፍል በመሄድ ቅብብሎች ይከውን የነበረበት መንገድ በራስ መተማመኑ ምን ያህል እያደገ እንደሄደ የሚያሳይ ነበር።

👉ዳዋ ሆቴሳ ቡድኑን መታደጉን ቀጥሏል

ሀዲያ ሆሳዕና ባህር ዳርን በገጠመበት እና ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት ነበር ዳዋ ከዱላ ሙላቱ የተሻገረለትን ኳስ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት የቀየረው። ዳዋ በመጀመሪያው ሳምንትም ቡድኑ 1-0 እየተመራ አንድ ግብ በማስቆጠር እና ሌላኛዋን ደግሞ አመቻችቶ በማቀበል ጥሩ የጨዋታ ጊዜ አሳልፎ ነበር። በሁለቱ ሳምንታት በወጥነት ተፅዕኗቸው ከታዩ ጥቂት ተጫዋቾች ውስጥም አንዱ ዳዋ ነው። የእርሱን ለየት የሚያደርገው ግን ቡድኑ በእንቅስቃሴ የተለየ የተዳሰዋል።ና እየፈጠረ ባልነበሩባቸው ጊዜያትም ጭምር በግል ብቃቱ ከሚፈጥራቸው ልዩነቶች የመጡ ዕድሎችን መጠቀም መቻሉ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ