ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፉት ሦስት ቀናት ተከናውነዋል። በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች መነሻነትም ሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን እና ምርጥ አሰልጣኝ ምርጫዋን እንሆ ትላለች።
አሰላለፍ: 4-3-3
ግብ ጠባቂ
መሐመድ ሙንታሪ – ሀዲያ ሆሳዕና
በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች ግብ ጠባቂዎችን የሚያስጨንቁ ሙከራዎች የተደረጉባቸው የግብ አጋጣሚዎች በብዛት አልተፈጠሩም። ሆኖም የሀዲያ ሆሳዕናው ሙንታሪ በተለይም የዜናው ፈረደን ጥብቅ ኳሶች ያዳነባቸው ቅፅበቶች ቡድኑ እስከመጨረሻው ግብ ሳይቆጠርበት እንዲዘልቅ ትልቅ እገዛ ነበረው።
ኃይሌ ገብረትንሳይ – ኢትዮጵያ ቡና
ኃይሌ በአንድ ለአንድ ግንኙነትች ወቅት የነበረው የበላይነት እንዲሁም ዓለምአንተ ተቀይሮ በመውጣቱ መሐል ሜዳ ላይ በፋሲል ተጫዋቾች የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድ ወደ መሐል እያጠበበ ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የቦታው ተመራጭ አድርጎታል።
አበበ ጥላሁን – ኢትዮጵያ ቡና
ኢትዮጵያ ቡና ፋሲልን 3-1 በረታበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ታፈሰ ሰለሞን ላስቆጠረው ግብ ከራሱ የሜዳ አጋማሽ በአስደናቂ እይታ ከተከላካዮች ጀርባ ለመሮጥ በተሻለ አቋቋም ላይ የነበረውን ታፈሰ ሰለሞንን ያገኘበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነበር። በጨዋታው አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ከመስጠት ባለፈ በጨዋታው እጅግ ወሳኝ የሆኑ የፋሲል ከነማን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማቋረጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ ነበር።
ተስፋዬ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
በሦስት የመሐል ተከላካዮች ጨዋታውን በጀመረው የሀዲያ ሆሳዕና ቡድን ውስጥ መሐል ላይ የተሰለፈው ተስፋዬ በቀለ ጥሩ ጨዋታ አሳልፋል። ስጋት የሚጭሩ ኳሶችን በቶሎ ከአደጋ ዞን በማራቅ እና ሳጥን ውስጥ የሚገኙ የባህር ዳር ተጫዋቾች በመቆጣጠር ለቡድኑ አሸናፊነት የራሱን ሚና ተወጥቷል።
አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና
በኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ የተሰለፈው ተጫዋቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የተዋጣለት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ከቀይ ካርዱ ወዲህ ከኃይሌ ገ/ተንሳይ ጋር በተለዋዋጭነት እንደ መሐል አማካይ በመሆን ሲሸፍኑበት የነበረው መንገድ ድንቅ ነበር። በተጨማሪም በሁለተኛው አጋማሽ ከመስመር እየተነሳ ወደ ጥልቀት ይልካቸው የነበሩት ኳሶች ውጤታማ ነበሩ ፤ ለማሳያነትም የአቡከር ናስር የፍፁም ቅጣት ምትም አሥራት በረጅሙ ከጣለው ኳስ የተገኘ ነበር።
አማካዮች
በረከት ወልዴ – ወላይታ ድቻ
በቁመቱ አጠር ቢልም የተከላካይ አማካይነት ሚናው የተዋጣለት ሆኗል። ተመሳሳይ ኃላፊነት ያለው ተጫዋች ከጎኑ ባልተሰለፈበት የአዳማው ጨዋታ ኳሶችን በመንጠቅ እና ከፊቱ ካሉ ፈጣሪ አማካዮች ጋር ጥሩ ቅንጅት በማሳየት ጨዋታው ለአዳማ አማካዮች እንዲከብድ ምክንያት ሆኗል።
ፉዓድ ፈረጃ – ሰበታ ከተማ
የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ከማድረግ አንስቶ ንቁ ሆኖ የዋለው ፉዓድ የመጀመሪያው ግብ የተቆጠረውም የእርሱ ቅጣት ምት የግቡን ቋሚ ለትሞ ሲመለስ በተፈጠረ ዕድል ነበር። ፉዓድ ሦስተኛውን ጎል ከመረብ በማሳረፍም የጨዋታው ምርጥ እንደነበር በግልፅ ማሳየት ችሏል።
እንድሪስ ሰዒድ – ወላይታ ድቻ
ኳሱን አቅልሎ በመጫወት እና ተጫዋቾችን በግል ክህሎቱ እያለፈ የተሳኩ ኳሶችን ለጓደኞቹ በማድረስ ድንቅ የጨዋታ ቀን አሳልፏል። በመጀመሮያው ጎል ላይ ጉልህ ድርሻ የተወጣው እና ሁለተኛውን የቡድኑን ግብም ጥሩ ዕይታውን በሚመሰክር አኳኋን ያቀበለው እንድሪስ ከኤልያስ አህመድ ጋር ያሳየው ጥምረት ለድቻ ቀጣይ ጨዋታዎችም ተስፋ የሆነ ነው።
አጥቂዎች
አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ በቀረበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበረው። የተሻለ ቀጥተኝነት ጨምሮ በቀረበው የሁለተኛ አጋማሽ የፈረሰኞቹ አቀራረብ ውስጥ አቤል ያለው ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው። አንድ ግብን በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው አቤል ሌላ ተጨማሪ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
ስንታየሁ መንግሥቱ – ወላይታ ድቻ
ለግላጋው የፊት አጥቂ ወላይታ ድቻን ባለድል ያደረጉ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ግቦቹን ያስቆጠረባቸው መንገድም የፊት አጥቂ ባህሪን የሚያሳዩ ነበር። ከአማካይ ተጫዋቾች ያገኛቸውን ኳሶች ይዞ ከግብ ጠባቂ ጋር በመገናኘት ቀለል ባለ አጨራረስ በስሙ ሁለት ግቦችን አስመዝግቧል።
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
ወጣቱ አጥቂ ትልቁን ኢትዮጵያ ቡና የግብ አስቆጣሪነት ኃላፊነት ተሸክሞ መጓዙን ቀጥሏል ። ፋሲል ከነማን 3-1 ሲረቱ አንድ ግብ ከማስቆጠር አልፎ ሀብታሙ ታደሰ ያስቆጠረውን ግብ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በተጨማሪም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ መሐል እየገቡ ሲጫወቱ የነበሩት የመስመር ተከላካዮች የሚተውትን ክፍት ቦታ ለመሸፈን ጉዳት አስተናግዶ እስከወጣበት ደቂቃ ድረስ የአቅሙን ሰጥቷል። በዚህም በተከታታይ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።
አሰልጣኝ – ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ለግማሽ የጨዋታ ጊዜ በሚባል ደረጃ ኢትዮጵያ ቡና በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ለመጫወት ቢገደድም ግቦችን አስቆጥሮ ባለድል እንዲሆን የአሰልጣኙ ሚና ከፍ ያለ ነበር። ውጤታማ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ እና ቡድኑን በማሸጋሸግ በጠንካራው ጨዋታ ላይ የገጠመውን ፈተና በአሸናፊነት መወጣት ችሏል።
ተጠባባቂዎች
ሰዒድ ሀብታሙ – ወላይታ ድቻ
ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ
ዓለማየሁ ሙለታ – ሰበታ ከተማ
ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ኤልያስ አህመድ – ወላይታ ድቻ
አዲስ ግደይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆሳዕና
© ሶከር ኢትዮጵያ