የ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውል ተራዘመ

ፌዴሬሽኑ የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውልን ማራዘሙን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ለወራት ያህል የማሰልጠን አጭር ኮንትራት ተሰጥቶት በ2012 ብሔራዊ ቡድኑን በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ብሩንዲን ከሜዳው ውጪ እና በባህር ዳር ዓለም አቀፍ በሰፊ ልዩነት ሲያሸንፍ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ቡድኑን መርቷል፡፡ ደደቢትን በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ያደረገው እና የሲዳማ ቡና ሴቶች ቡድንን የመራው አሰልጣኙ ሐምሌ 30 ቀን 2012 ውድድር በኮሮና ምክንያት በአህጉሪቱ ባለመኖሩ ፌድሬሽኑ በወቅቱ ውል እንደማይራዘም የገለፀ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የአንድ ዓመት ውል በማቅረብ አራዝሞለታል፡፡

አሰልጣኝ ፍሬው ዛሬ በይፋ ይፈራረም እንጂ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ አዳማ እና ሀዋሳ እየተደረገ ባለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮችን በስፍራው ተገኝቶ እየተመለከተ ሲሆን በቅርቡም ለሠላሳ ተጫዋቾች ጥሪን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ፊፋ በኮሮና ምክንያት የዓለም ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ውድድሮችን ለመሰረዝ ከውሳኔ መድረሳቸው ታውቋል። በዚህም አህጉራዊ የማጣርያ ውድድሮች እንደተሰረዙ ካፍ አረጋግጧል። ይህን ተከትሎም ብሔራዊ ቡድኑ በአንደኛ ዙር ማጣርያ ከዚምባብዌ ጋር የሚያርገው ጨዋታ በመሰረዙ እጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል በቀጣይ የሚጠበቅ ጉዳይ ይሆናል። ምናልባትም እንደ ወንዶች ከ17 ዓመት እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች ሁሉ የሴቶቹንም ለቀጣይ ውድድሮች ለማዘጋጀት ያለመ ኮንትራት እንደሚሆን ይገመታል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ