አዲስ በሚዘጋጀው የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች መለያ ዙርያ ውይይት ተደረገ

ለሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች መለያ ለመግዛት አዲስ ሀሳብ ይዞ የመጣው ቤትኪንግ ዛሬ ከክለብ አመራሮች ጋር ውይይት አደረገ።

የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለጊዜው ባልተገለፀ ከፍተኛ ገንዘብ የስያሜ መብቱን የገዛው ቤትኪንግ ለ13 ክለቦች የሚለብሱትን ማልያ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት በራሱ ወጪ ሊገዛ እንደሆነና በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር ለዛሬ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የክለብ ሥራ አስኪያጆች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን መዘገባችን ይታወቃል።

በዛሬው ስብሰባ ዙርያ ከተጠናቀቀ በኋላ ባገኘነው መረጃ ሁሉም ክለቦች ሦስት የተለያዩ የማልያ ናሙናዎች በቅርብ ቀናት ውስጥ ይዘው እንዲመጡ ተነጋግረው ይዘውትም በሚመጡት መለያቸው ውስጥ አስቀድመው ክለቦቹን ስፖንሰር ያደረጉት ተቋማት በመለያው ላይ እንደሚካተቱ እና በእያንዳንዱ መለያ የቤትኪንግ አርማ እንደሚኖር ተስማምተው ተለያይተዋል። ይዘውት የመጡት ሦስት ናሙናዎች ቤትኪንግ የአዲስ አበባው የውድድር ጊዜ (እስከ ስድስተኛ ሳምንት) ሳይፈፀም ማልያውን አጠናቆ ሊያስረክብ እንደሚችልም ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ