ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የሊጉ የረጅም ጊዜ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ቡድኖችን የሚያገናኘውን የነገ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን አንስተናል።

ሀዋሳ ከተማ ደካማ አጀማመሩን ከማቅናት ባለፈ ለቀጣይ ሳምንታት የሚሆን የስነ ልቦና ስንቅ የሚሸምትበት አልያም የውጤት እጦቱን የሚያባብስበትን ጨዋታ ነገ የሚያደርግ ይሆናል። ቡድኑ የተሻለ ልምድ አላቸው የሚባሉ ተጫዋቾቹን ይዞ ወደ ሜዳ መግባት በቻለበት የጊዮርጊሱ ጨዋታም ተዳክሞ ታይቷል። የኋላ መስመሩ ለፈጣን አጥቂዎች የተጋለጠ ሆኖ መታየቱ ደግሞ እንደነገው ዓይነት ጨዋታዎች ላይ መቸገሩን እንዳይቀጥል የሚያሰጋ ሆኗል። መሀል ሜዳ ላይም በተጋጣሚ የአማካይ ክፍል የሚወሰድበት ብልጫ ፈጣኖቹን የፊት አጥቂዎች ያለ በቂ ዕድል ሲያስቀራቸው ይታያል። አልፎ አልፎ የሚገኙ መልካም ዕድሎችንም ወደ ግብ ለመቀየር አለመቻሉ ከኋላ ኳስ የሚመሰርተው የነገ ተጋጣሚው በራሱ ሜዳ ላይ የሚሰራቸውን ስህተቶች በመጠቀም ረገድ ዕንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። በሌላ በኩል በሦስተኛው ሳምንት የቡድኑ ጨዋታ በመስመር አጥቂነት ዮሀንስ ሴጌቦ ያሳየው እንቅስቃሴ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድን ተስፋን የሚጭር ነው። በማጥቃት መስመሩ ላይ የዮሃንስ በልበ ሙሉነት ከተከላካዮች ጋር የመጋፈጥ እንዲሁም በቀጥታ ሙከራዎችን የማድረግ ድፍረት መስፍን ታፈሰም ለነገ የሚደርስ ከሆነ ቡድኑ ፊት ላይ የተሻለ ለውጥ ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል።

ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ያሳካው ኢትዮጵያ ቡና በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንደሚዘልቅ የሚያሳይበትን ድል ለማግኘት ሀዋሳን ይገጥማል። በአወዛጋቢው የድሬዳዋ ጨዋታ አሸንፎ መውጣት የቻለው ኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት አጥቶም ሦስት ነጥቦችን ማስካቱ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው። በአንፃራዊነት ደከም ብለው ከታዩ ቡድኖች መካከል የሆነው ሀዋሳ ከተማን መግጠሙ አሸንፎ የመውጣት ግዴታ ውስጥ ስለሚከተው ግን ጨዋታውን በጫና ውስጥ ሆኖ ሊያደርግ ይችላል። በድሬዳዋው ጨዋታ ኳስ ከኋላ መስርቶ ሲወጣ የሚፈጠርበትን ጫና በመቅረፉ ረገድ እንደቀደሙት ጨዋታዎች ያልነበረው የቡድኑ የመሀል ክፍል በአንፃሩ ከመስመር ተከላካዮች ጋር የሚከውናቸው ቅብብሎች ክፍተቶችን ሲያስገኙለት ታይቷል። ለነገው ተጋጣሚውም መሀል ላይ ተጫዋቾችን በርከት አድርጎ ለጨዋታው ሊቀርብ መቻሉ በቡና በኩል ተመሳሳይ ግብረ መልስ እንድንጠብቅ የሚያደርግ ነው። በሌላ በኩል ፊት ላይ የሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መምጣት ወደ መጨረሻ ዕድልነት ተቀይረው የሚባክኑ ካሶችን ውጤት ላይ በማዋሉ በኩል ለቡድኑ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በዚህ ላይ የአቡበከር ናስርን ግልጋሎት በሙሉ ጤንነት የሚያገኝ ከሆነ የቡድኑ የፊት መስመር ስልነት እንደሚጨምር ይታሰባል።

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ያልነበረው ምኞት ደበበን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ በኮቪድ ምክንያት በቡድኑ ውስጥ ያልነበሩ ሁለት ተጫዋቾችም አገግመውለታል። በሌላ በኩል የቡድኑ ቁልፍ አጥቂ መስፍን ታፈሰ እና ተባረክ ኢፋሞ መድረስ አጠራጣሪ ሲሆን ሀብታሙ መኮንን በጉዳት አለልኝ አዘነ በቅጣት ከኃይቆቹ ስብስብ ውጪ ናቸው። ተመስገን ካስትሮን በቅጣት በሚያጣው የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ውስጥ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ኢብራሂም ባዱ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። አቤል ማሞ ፣ ወንድሜነህ ደረጀ እንዲሁም የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች አቡበከር ናስር ከጉዳት መመለስ ለቡና መልካም ዜና ሆኗል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረበት 1990 ጅምሮ ሳይወርዱ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች ከየትኛውም ቡድን በበለጠ 42 ጊዜ ተገናኝተዋል።

– የእርስ በእርስ ውጤታቸው በመሀላቸው ያለውን የፉክክር ሚዛናዊነት የሚያሳይ ነው። በእስካሁኑ የ42 ጊዜ ግንኙነታቸውም በ16 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 14 ሀዋሳ ደግሞ 12 ጊዜ ድል አስመዝግበዋል።

– በጥቂት አጋጣሚዎች ካልሆነ በቀር ጎል የማያጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 95 ጎሎች ሲቆጠሩበት ኢትዮጵያ ቡና 52 ጊዜ ኳስ እና መረብን በማገናኘት የበላይ ነው። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሦስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 43 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሜንሳህ ሶሆሆ

ዳንኤል ደርቤ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

ሄኖክ ድልቢ – ጋብርኤል አህመድ – ኤፍሬም ዘካሪያስ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – ዮሀንስ ሴጌቦ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማሪያም ሻንቆ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ዓለምአንተ ካሳ – አማኑኤል ዮሃንስ

አቤል ከበደ – ሀብታሙ ታደሰ – አቡበከር ናስር


© ሶከር ኢትዮጵያ