ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

የቡና እና የድሬዳዋን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል። ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ጎሎችን ጨምሮ በሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ድሬዳዋን ይገጥማል። ተመስገን ካስትሮን በቀይ ባጡበት ጨዋታ ጥሩ መነሳሳት ያሳዩት ቡናማዎቹ በተመሳሳይ መንፈስ ወደ ሜዳ መግባት እንደ ወልቂጤው ጨዋታ በትኩረት ማጣት ዋጋ ከመክፈል የሚያድናቸው ጉዳይ ነው። በፋሲሉ ጨዋታ ከራሳቸው የሜዳ ክልል ኳሶችን መስርቶ የተጋጣሚን አጥር አልፎ በመውጣት የተሻለ ስኬት ያሳየው ቡድኑ አልፎ አልፎ ድንገተኛ ረጅም ኳሶችን የመጠቀም ባህሪውም የግብ ዕድል ሲፈጥርለት ተስተውሏል። በነገው ጨዋታም ተጋጣሚው መሀል ሜዳ ላይ ተጫዋቾችን በማብዛት የኃላ መስመሩ ላይ ጫና ሊፈጥር ከመቻሉ አንፃር መሰል መፍትሄዎችን ጥቅም ላይ ሊያውል እንደሚችል ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ በማጥቃቱ ረገድ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች አጠቃቀም መልካም ሆኖ መገኘት ለነገው ዓይነት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ በቁጥር በልጦ መገኘት ወሳኝ በሆነባቸው ጨዋታዎች ላይ እጅግ ወሳኝ ይሆናሉ። የታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣትም ከአማካዮች ግብ ማግኘት ከመጀመር አንፃር ለቡድኑ መልካም ዜና ተደርጎ የሚወሰድ ነው። የመጀመሪያ የሊግ ድሉን ለማግኘት ወደ ሜዳ ለሚገባው ድሬዳዋ ከተማ የነገው ጨዋታ ውጤት መጪውን ጊዜ ከመወሰን አንፃር ወጣኝ ሊባል የሚችል ነው። በኤልያስ ማሞ የፈጠራ ብቃት ላይ ጥገኛ እንደሆነ እየታየ ያለው ቡድኑ ፊት መስመር ላይም ግብ የማስቆጠር ችግሩ በተደጋጋሚ እየታየ ነው። የቡድኑ ዋና አጥቂ ጁኒያስ ናንጄቦ በአስደናቂ ፍጥነት ተከላካዮችን ጥሶ ከኳስ ጋር አደጋ ዞን ውስጥ የመግባት ችግር ባይኖርበት የመጨረሻ ውሳኔዎቹ ግን ለድሬ ግቦችን ሊያመጣ አልቻለም። እንደ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ሁሉ ድሬዎች ነገም አምስት አማካዮችን በመጠቀም ተጋጣሚያቸው ወደ ፊት ለመሄድ ክፍተቶችን እንዳያገኝ ለማድረግ እንደሚጥሩ ይታሰባል። ከዚያ ውጪ ቡድኑ የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይም ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል ይታሰባል። ድሬዎች በማጥቃቱ ረገድ የቡናን የማጥቃት ሂደት በሚያጨናግፉበት ቅፅበት ኳሶችን በቶሎ ወደ ፈጣኑ አጥቂያቸው ማድረስ ከቻሉ አደጋ የመፍጠር አቅሙ እንዳላቸው ይታመናል። በሶከር ኢትዮዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድኖች ውስጥ በተከታታይ ሳምንታት መግባት የቻለው አቡበከር ናስር ነገም ከግራ መስመር በመነሳት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚጠበቅ ሲሆን መሀል ሜዳ ላይ ኤልያስ ማሞ ከአማኑኤል ዮሃንስ የሚገናኙባቸው ቅፅበቶችም ተጠባቂ ይሆናሉ። የድሬው ሙኸዲን ሙሳ እንዲሁም የቡናው ሀብታሙ ታደሰ የሳምንቱን ግብ አስቆጣሪነታቸውን ይቀጥሉበት እንደሆንም ጨዋታው የሚያሳየን ይሆናል። በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡናው ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ ፤ ባለፈው ሳምንት በጉዳት ያልነበሩት ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ እና ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጄ ከጉዳታቸው አገግመዋል ፤ በፋሲሉ ጨዋታ ቀጥታ ቀይ ካርድ የተመለከተው ተመስገን ካስትሮ ደግሞ የሦስት ጨዋታ ቅጣቱን በዚህኛው ጨዋታ ይጀምራል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት ሪችሞንድ አዶንጎ እና ኢታሙና ኪይሙኒ ከጉዳታቸው ቢያገገሙሞ ከነገው ጨዋታ ስብስብ ውጪ ተደርገዋል ፤ በተጨማሪም ረመዳን ናስር ከቡድኑ ጋር ልምምድ መስራት የጀመረ ቢሆንም የኮቪድ ምርመራ ስላልተደረገለት የማይደርስ ሲሆን ጉዳት ላይ የነበረው ኩዌኩ አንዶህ ግን ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ስላገገመ በነገው ጨዋታ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል። እርስ በርስ ግንኙነት – ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ16 ጊዜያት ያህል ተገናኝው ኢትዮጵያ ቡና ገሚሱን (8) በማሸነፍ የበላይ ሲሆን 5 ጊዜ አቻ ተለያይተው በ3 አጋጣሚዎች ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል። – በ16ቱ ግንኙነቶች 39 ጎሎች ሲቆጠሩ 25 ጎሎች ቡናማዎቹ ያስቆጠሯቸው ናቸው። ቀሪዎቹ 14 ጎሎችን ብርቱካናማዎቹ አስቆጥረዋል። ግምታዊ አሰላለፍ ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3) ተክለማርያም ሻንቆ ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሀንስ – ዓለምአንተ ካሳ አቤል ከበደ – ሀብታሙ ታደሰ – አቡበከር ናስር ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1) ፍሬው ጌታሁን ኩዌኩ አንዶህ – ፍቃዱ ደነቀ – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ ኢሳይያስ አስጨናቂ ሉቃስ – ዳንኤል ደምሴ ጁኒያስ ናንጄቦ – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ ሙኸዲን ሙሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ