የአሠልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 ሀዋሳ ከተማ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዴት እንቆጣጠር የሚለውን ተነጋግረን ነበር። በተለይ ደግሞ የመስመር ላይ እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር አስበን ነበር። ግን ያንን ማድረግ ሳንችል ጊዮርጊሶች በመስመር ላይ አጥቅተውን ግቦችን አስቆጥረውብናል። ከጨዋታ ጨዋታ ከኳስ ጋር ያለን ነገር እየተሻሻለ ነው ብዬ አምናለው። ይህ ቢሆንም ግን እንደ ቡድን አልተደራጀንም። ለቀጣዩ ጨዋታ ግን ጠንክረን እንቀርባለን።

የመስፍን ታፈሰ አለመኖር…

መስፍን ወጣት ተጫዋች ነው። ቢኖር በጣም ያግዘን ነበር። ዛሬ አለመኖሩም ክፍተቶች ፈጥሮብናል። ግን የእርሱን አለመኖር በሌሎች ተጫዋቾች ተክተናል።

ማሒር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቡድኑ ሁለተኛ ድሉን ስለማግኘቱ…

ከጨዋታው በፊት እንዳለኩት ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ ለእኛ ወሳኝ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ግቦችንም አስቆጥረናል። ጨዋታው ከፍታ እና ዝቅታዎች ቢኖሩትም እኛ ግን ብዙ አዎንታዊ ነገሮችን አግኝተንበታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ስለተወሰደባቸው ብልጫ..

የመጀመሪያው ነገር በእኛ በኩል የነበረውን ፍጥነት በማጣታችን ነው። ሁለተኛው ደግሞ ወደ ኋላ ማፈግፈጋችን ነው። ግን ሦስተኛ ጨዋታችን መሆኑ እና በፀሀያማ ሰዓት በመጫወታችን ለተጫዋቾቻችን ከባድ አድርጎታል። ምንም ቢሆን ግን አራት ግቦችን ማስቆጠራችን እና ጨዋታውን እንደጨረስን ማሰባችንም ሊሆን ይችላል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ የተወሰደብን። በአጠቃላይ ግን በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነገሮችን አይተናል። እነዚህንም ነገሮች አጠናክረን እንቀጥላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ