የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 3-2 ድሬዳዋ ከተማ

ከቡና እና ድሬዳዋ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ጉልበት የበዛበት ጨዋታ ነበር፤ እንዴት ነበር ለአንተ ?

“አዎ የተወሰኑ ፋዎሎች ነበሩ። የመጀመሪያው ግማሽ ላይ በተከፈተው ቦታ ለመሄድ ነው የሚያስቡት። የዛ ዓይነት ዕድል ሲፈጥሩ የእኛ ልጆች ላይ የመረጋጋት ነገር አልነበረም ፤ ያንን ክፍተት እንዴት ነው መድፈን ያለብን ? እነሱ እንዳይጠቀሙበት ኳሶቻችን እንዳይበላሹ የሚለው ላይ። ሜዳውም አመቺ አይደለም ፤ ሊታሰብበት ይገባል። ራሱን የቻለ ነጣቂ ነው ሜዳው። የእኛ ልጆች ነፃ ሰው ያገኛሉ ግን እሱን ከመጠቀማቸው በፊት ተቃራኒ ተጫዋች ይደርስባቸዋል። ለእኔ ምንም አስቸጋሪ ነገር አልነበረውም ግን በተፈጠረው ክፍተት ተጋጣሚ ሲሄድ ልጆቻችንን የረበሻቸው ይመስለኛል።”

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ኃይል ለመብዛቱ ምክንያቱ ምን ይመስልሀል ?

“እኛ ልጆች ላይ ብዙ ያየሁ አልመሰለኝም። ይመስለኛል ሁለቱም በሁለት ቢጫ ነው የወጡት። ያ እንግዲህ የዳኞቹ ውሳኔ ነው።”

ዳኝነቱን እንዴት አገኘኸው ?

“ጥሩ ነው እንግዲህ። እኔ ሁሌም የምለው ከእነሱ እይታ የተሰወረ ነገርም ስለሚኖር በሌላው ነገር እስከሚታገሱ ዳኞቻችን መታገስ ያስፈልጋል። ርቀት ላይ ስለነበርኩ ጥፋት ተፈፅሟል አልተፈፀመም ለማለት ትንሽ አስቸጋሪ ነው።”

አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

በተደጋጋሚ ከአራተኛ ዳኛው ጋር ትነጋገር ነበር ፤ ምክንያቱ ምን ነበር ?

“ዳኝነቱ ልክ አይደለም በአጠቃላይ ፤ በጣም ነው የሚያሳዝነው። በ ዲ ኤስ ቲቪ እየታየ እንኳን በሥነ ስርዓት አይዳኙም እንዴ ? በጣም ነው የማዝነው። ፍፁም ቅጣት ምት እኛን ይከለክላሉ ለእነሱ ግን ይሰጣሉ። እንዴት ነው ታድያ ማሸነፍ የሚቻለው ? ብቻ በጣም ያሳዝናል።”

ዳኝነቱ ሙሉ ለሙሉ ቡድኔን ጎድቶታል ነው የምትለው ?

“አዎ በትክክል ! የአሁኑ ፍፁም ቅጣት ምት ነው እንዴ ? የመጀመሪያውን ለምን አልሰጠንም ? እኛ ላይ የተሰጠውስ ቢሆን ያሰጣል ? እንደዚህ ዓይነት ስራ እየተሰራ እንዴትስ ነው ለማሸነፍ የምንመጣው ? ቡድኔን አወረደው። ሁለተኛ እሱ ጨዋታውን መቆጣጠር ባለመቻሉ ጨዋታው ወደ ኃይል ሄደ። ሁለቱም በድኖች ጥሩ ጨዋታ ነበር የሚጫወቱት የነበረው።ከዛ በኃላ ያለው ነገር ተበላሸ።”

ለሁለቱ ቀይ ካርዶች መነሻው የዳኛ ውሳኔ ነው ትላለህ ?

“ልጆቹን ወደ መጥፎ ነገር እንዲገቡ አደረጋቸው። እንዲረጋጉ አላረጋቸውም። እኛ ላይ ቢጫ ይሰጣል ለእነሱ አይሰጥም። ለሁሉ ነገር ጥፋተኛ እኛን አደረገ ስለዚህ ልጆቹ ወደማይሆን ነገር ውስጥ ገቡ። በዚህ ምክንያት ሁለት ሰው በቀይ ሊወጣ ቻሏል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ