ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ፋሲል ከነማ

አጭር እና ረጅም የዝግጅት ጊዜ ያሳለፉት ቡድኖች የሚገናኙበትን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

በአነጋጋሪ ክስተቶች እና በሽንፈት ሊጉን የጀመረው ጅማ አባ ጅፋር ከወልቂጤ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ በኋላ ከባዱን ፍልሚያ ነገ ያከናውናል። አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው እንዳሉትም ቡድኑ ካሳለፈው ከባድ ጊዜ አንፃር አንድ ነጥብ ማሳካቱ ወጥፎ የሚባል አልነበረም። ያም ቢሆን ከፋሲል ጋር በሚኖረው ጨዋታ በብዛት በአዳዲስ ተጫዋቾች ከተዋቀረው ጅማ የተሻለ መናበብን ማግኘት የግድ ይለዋል። የነገ ተጋጣሚው የኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ የሚጫወት ከመሆኑ አንፃርም ጅማ ወደራሱ የሜዳ ክልል ተገፍቶ ለመቆየት እና ነጥብ የመጋራት አዝማሚያ ካለውም ሙሉ ለሙሉ ወደ ኋላ ተስቦ ጥንቃቄ ተኮር እንቅስቃሴ ሊያደርግ የሚችልባቸው ደቂቃዎች ሊረዝሙ እንደሚችሉ የሚገመት ነው። የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር በጉልህ የታየበት ከመሆኑ አንፃርም በቁጥር ጥቂት ቢሆኑ እንኳን የሚፈጥራቸውን የግብ አጋጣሚዎች መጨረስ እንደ ተመስገን ደረሰ ካሉ አጥቂዎቹ የሚጠበቅ ነው። የአሰልጣኝ ጳውሎስ ስብስብ ያሉበትን በርካታ ክፍተቶች ከመቀነስ አንፃር በወልቂጤው ጨዋታ ያልተጠቀማቸውን ሌሎች ፈራሚዎቹን ይዞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን ከቀናት በፊት በወልቂጤ ከተማ በኩል የተጫዋች ተገቢነት ክስ እንደተነሳበትም መስማታችን አይዘነጋም።

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተሳታፊ በመሆኑ የተሻለ የጨዋታ ዝግጁነት ኖሮት ጥሩ አጀማመር ያሳየው ፋሲል በቡናው ጨዋታ ደግሞ ወርዶ ታይቷል። በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ በተፎካካሪነቱ የዘልቃል ተብሎ ከሚጠበቅ ቡድን አንፃርም በቶሎ ወደ አጀማመሩ መመለስ ይኖርበታል። ይህንን ለማድረግ በንፅፅር ቀለል ያለ እና ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኝ ቡድን ጋር መገናኘቱ ተጠቃሚ የሚያደርገው ቢሆንም በከፍተኛ የቡድን ተነሳሽነት ወደ ሜዳ መግባት ግን እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። በተቃራኒው ሲታይ ደግሞ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አለማሳካት ቡድኑን ጫና ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ግልፅ ነው። ከዚህ አንፃር የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች አበራክቶ እና በቶሎ ግብ ለማስቆጠር በፈጣን እንቅስቃሴ ጨዋታውን እንደሚጀምር ይገመታል። በግል ክህሎታቸው ጥሩ የሚባሉ አማካዮችን የያዘው ፋሲል እንደ ኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ሁሉ በዚህ ጨዋታም በቂ ክፍተት እንደልብ ለማግኘት ሊቸገር የሚችል በመሆኑ ከቦታው ተሰላፊዎች ምርጥ ብቃትን ይጠብቃል። ከዚህ በተጨማሪም ቁልፍ ቦታዎች ላይ የሚያገኛቸውን የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ማስተካከል እና ለመልሶ መጠቃት የሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎችን በአግባቡ ለመቆጣጠር መሞከር ከዐፄዎቹ ይጠበቃል።

ጅማ አባ ጅፋር ጉዳት ላይ የነበረው ተከላካዩ ከድር ኸይረዲን ዛሬ ለብቻው ቀላል ልምምድ መስራት ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ አይደርስለትም። ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪም በቀጥታ ቀይ ካርድ ቅጣት ሁለተኛ ጨዋታው ያልፈዋል። በፋሲል ከነማ በኩል የተመዘገው ብቸኛ ጉዳትም የተከላካዩ ሰዒድ ሁሴን ብቻ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተው ጅማ አባ ጅፋር ምንም አላሸነፈም። የ2011ዱን የ6-1 ድል ጨምሮ ፋሲል 7 ጎሎችን ሲያስቆጥር ጅማ አንድ ግብ ፋሲል ላይ አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ

ትርታዬ ደመቀ – ንጋቱ ገብረስላሴ – ሱራፌል ዐወል

ተመስገን ደረሰ – ብዙዓየሁ እንዳሻው – ሳዲቅ ሴቾ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

በረከት ደስታ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ