በክለቦችን ትርፋማነት ዙርያ የውይይት መድረክ ተካሄደ

ክለቦች ትርፋማ የባለቤትነት ድርጅታዊ መዋቅር እንዲኖራቸው ለማስቻል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀው የውይይትና አቅጣጫ የማስያዝ መርሐግብር በጁፒተር ሆቴል ተካሄደ።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው በዚህ መድረክ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደን አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ ዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም የሊግ ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ተገኝተዋል። በጉባዔው ላይም አስራ ሦስቱ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች በሥራ አስኪያጃቸው እና በተወካዮቻቸው አማካኝነት በመድረኩ ታድመዋል።

ከጠዋት 03:00 ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል በተካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ለአቶ ኢሳያስ ጅራ በመክፈቻ ንግግራቸው ” ክለቦቻችን የመንግስት ጥገኛ መሆናቸው ይታወቃል። ይህ መድረክ እንዲዘጋጅ የታሰበበት አላማ ፌዴሬሽኑ የሚታየው ስጋት ስላለ ነው። እንደምታስታውሱት የሊግ ኩባንያው እንዲቋቋም ስንፈልግ በደንብ አስበንበት የተነሳነው ብዙ ፈተናዎች አልፈን ዛሬ በአንድ ዓመት ውስጥ በደረሰበት ደረጃ ስንመለከት ደስተኛ ሆነናል። እንደዚሁ ይህ መድረክ የተዘጋጀው ክለቦችን የመንግስት ጥገኛ ናቸው። መንግስት የሚሰጠውን 50 ሚሊዮን ብር እየጨረስን እስከ መቼ ነው የምንጓዘው? ይህ አያዋጣም። ስለዚህ ክለቦች ከትንሽ ነገር ተነስተው ገንዘብ የሚያፈራ ሀብት መፍጠር ይገባቸዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ረገድ አቅሙን ለማጠናከር እየሄደበት ያለው መንገድ የሚያስመሰግነው ነው። ሌሎችም ክለቦች ጠንክረን በመስራት ክለቦች አትራፊ እንዲሆኑ ይህ ስልጠና ተዘጋጅቷል። ይህ ስልጠና በከፍተኛ ሀገራዊ ፍቅር እንዲሰጥ ላደረጉት ለዶ/ር ጋሻው ምስጋና አቀርባለሁ።” ብለዋል።

በማስከተል የመድረኩ አወያይ የሆኑት ያለፉትን ሀያ ዓመታት በስፖርት ቢዝነስ ባለሙያ እና አማካሪ እንዲሁም በአሜሪካ በታውሰን ዩንቨርስቲ መምህር በሆኑት እና የተለያዩ የአውሮፓ ክለቦችን በሚያማክሩት ዶ/ር ጋሻው አብዛ ከታሳታፊ ክለቦች ጋር ትውውቅ ካደረጉ በኃላ ለውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።

የመድረኩ መዘጋጀት ዋና ዓላማ

ክለቦቻችንን ከመንግስት ድጎማ ተላቀው ራሳቸው ባለቤት ሆነው አትራፊ እንዲሆኑ ማስቻል ሲሆን ለዚህም በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ የሚገኙ ክለቦች ምን ዓይነት አስተዳደራዊ መዋቅር አላቸው? ክለቦቹን ማነው በባለቤትነት የሚመራቸው? የሚለውን የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ የኢትዮጵያ ክለቦች ወደ ራሳቸው ባለቤትነት እንዲገቡ ማስገንዘብ የስልጠናው ዓላማ ነው።

የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ

“የአውሮፓ ሀገራት ስንመለከት በአጠቃላይ 55 ሊጎች 712 ክለቦች አሉ። አንዳቸውም የመንግስት ክለብ አይደሉም። እነዚህ ክለቦች በሁለት የተከፈለ የባለቤትነት አስተዳደር ይመራሉ። አንደኛው በግል ባለሀብት (በግለሰቦች) ሁለተኛው በህዝብ ንብረትነት (በደጋፊዎች) የሚተዳደሩ ናቸው። መነሻቸው ከተለያዩ ትናንሽ የገቢ ምንጮች ሆነው በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ትርፋማ የሆነ ክለብ መምረጥ ችለዋል።

አፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ሊጎች ስንመለከት በሦስት የተከፈለ የአስተዳደር መዋቅር አላቸው። የመንግስት፣ የባለሀብት እና የህዝብ ክለቦች ይገኛሉ። በአፍሪካ እግርኳስ ውስጥ በቻምፒዮንስ ሊግ፣ በኮፌዴሬሽን ካፕ፣ ውጤታማ በመሆን ከፍተኛ ስም ያተረፉ የግብፅ፣ የሞሮኮ፣ የቱኒዚያ፣ አልጄሪያ ክለቦች አብዛኛዎቹ በህዝብ ወይም በግል ባለሀብት የሚተዳደሩ ክለቦች ናቸው። ከዚህ ውጭ በአፍሪክ የክለቦች መድረክ ስኬታማ አይሁኑ እንጂ የደቡብ አፍሪካ በአብዛኛው ክለቦች በህዝብ እና በግል ባለሀብት የሚተዳደሩ ትልቅ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ክለቦች አሉበት።

ምስራቅ አፍሪካ ለምሳሌ ኬንያ 16 የሊግ ክለቦች ውስጥ 5 የህዝብ 4 የመንግስት 7 የግል ባለ ሀብት የሚተዳደሩ ክለቦች ናቸው። በተመሳሳይ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ መሰል የሆነ ተሞክሮ አላቸው።

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ካሉት አስራ ስድስት የሊግ ክለቦች ውስጥ ከሁለቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ውጭ አብዛኛዎቹ ከከተማ አስተዳደር የሚደጎሙ ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ረገድ ለሁሉም ክለቦች ተሞክሮ የሚሆን አክስዮን ማኅበር መስርቶ አንቅስቃሴ መጀመሩ ለሀገራችን እግርኳስ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው።

ከሻይ እረፍት በኃላ የሀገራችንን ክለቦች ውስጣቸው ያሉ ፈተናዎች እና ችግሮች በተዘጋጀው ሰባት ነጥብ መጠይቅ ዙርያ ለ45 ደቂቃ የፈጀ በጉሩፕ የተከፋፈለ ውይይት ተደርጓል።

የቡድን ውይይቱ እንደተጠናቀቀ በቡድን መሪዎቹ አማካኝነት የደረሱበትን ድምዳሜ አብራርተዋል። ክለቦቹ ያሉባቸውን ችግሮች ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት

* ራዕይ አቅም ያለው የስፖርት መሪ አለመኖር። የክለብ አስተዳደር ሹመኞች እና የመንግስት ፖለቲካ አመራር መሆናቸው።

* የክለቦች አስተዳደራዊ መዋቅር አደረጃጀት የተሟላ አለመሆን እና ለስፖርት የሚመጥን በብቁ ባለሙያ ያልተደራጀ መሆኑ እና የዘልማድ አሰራር መበርከት

* ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ እጥረት

* ክለቦቹ የራሳቸው የልምምድ ሜዳ እና የመጫወቻ ስታዲየም አለመኖር

* በርከት ያሉ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን ወደ ገንዘብ የመቀየር ችግር። እንዲሁም ደጋፊውን መኪና አበል ወጪ ችለው ክለባቸውን እንዲደግፉ ማድረግ ትልቅ ችግር ነው።

* የአንድን ክለብ የሥራ እንቅስቃሴ አንድ ሰው ብቻ ሁሉን ነገር ደርቦ እንዲሰራ ማድረግ

* የክለቦች መተዳደርያ ደንቡ የመንግስት አመራሮች እንዲያቅፍ የተሰራ መሆኑ እና ከስፖርት ኮሚሽኖች ጋር የተሳሰረ መሆኑ

* በወጣት ታዳጊዎች ልማት ላይ የታሰበውን ያህል ሥራ እየተሰራ አለመሆኑ እና ሁሉም ክለቦች በተጫዋች ግዢ ላይ ብቻ ማተኮራቸው።

* ክለቦች የፋይናስ ግልፅነት ችግር አለ አሰራሩ ሁሉም የሚያቀው ግልፅነት የሰፈነበት የፋይናስ ፍሰት የለም። ባህላዊ አሰራር ይበዛበታል።

* ከመንግስት ከሚሰጥ ድጎማ ውጭ ሌሎች ገንዘብ የሚገኝባቸውን የማርኬት የስፖንሰር የማፈላለግ ሲስተም ሥራ አለመስራት። የክለቦች ትኩረት ዓመት ጠብቆ ውድድር ማድረግ ብቻ መሠረታዊ ችግር ነው።

* ለሰለጠኑ ባለሙያዎች በቂ ክፍያ ክለቦች አለመክፈል ባለሙያዎች እየሸሹ መሆናቸው አንዱ ችግር ነው።

በመጨረሻም ለዚህ ዋናዋና ችግሮች መፍትሔ ያሏቸውን በርከት ያሉ ሀሳቦች ያስቀመጡ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ገልብጦ እራስን ከሁኔታዎች ጊዜው ከሚጠይቀው ነገር ጋር እራሳቸውን ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲገቡ ማድረግ መፍትሔ እንደሆነ ጉባያተኛዎቹ ተናግረዋል።

ዶ/ር ጋሻው አብዛ በማስከተል በቀረበው ችግሮች እና መፍትሔዎች ዙርያ ጠቅለል ያለ ሀሳብ ሰጥተዋል። በተለይ የክለቦች የፋይናስ አቅም ለማጠናከር እና ትርፋማ የባለቤትነት (ፕራይቬታይዜሽን) መዋቅር እንዲኖር ለማስቻል። ከመንግስት ዱጎማ እንዲላቀቅ ከታሰበ ሦስት የመፍትሔ ሀሳቦችን አስቀምጠዋል

*መንግስት 30% ወስዶ 30% የግል ባለ ሀብት እንዲዘው ቢደረግ እና 40% ደግሞ የተመዘገበው ደጋፊው እንዲመራው ቢደረግ።

*49% መንግስት እንዲይዘው አድርጎ 51% ለተለያዮ ተቋማት ባለ ሀብት ለመሸጥ ቢቻል።

* 49% ባለ ሀብት ይዞት 51% ደጋፊው(ህዝቡ) ቢመራው የክለቦችን ከመንግስት ጥገኝነት ነፃ እንደሚወጡ ማድረግ እንዲቻል ገልፀዋል። ይህን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል የተማረ የሰው ኃይል እና ክለቦች ተቋማዊ አደረጃጀታቸውን መቀየር ከቻሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ክለቦች ትርፋማ የባለቤትነት ድርጅታዊ መዋቅር መፍጠር ይችሏሉ ብለዋል። ይህ እንዲሆንም በቀጣይ ተመሳሳይ የስልጠና መድረኮች ይዘጋጃሉ ተብሏል።

“የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ በላይ ክለቦች እራሳቸውን እንዲችሉ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራው ስራ ውጭ ሌላ ተግባር የለውም። ስለዚህ ደፍረን ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባና የሚመጡ ፈተናዎችን መጋፈጥ እንደሚያስፈግ መግለፅ እወዳለሁ። የሊግ ካምፓኒ ምስረታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚሄድበት እንቅስቃሴ በጎ ምሳሌ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆኑ ናቸው” ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ጠቃሚ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ይህ መድረክ ቀጣይነት እንዲኖረው ሰባት አባላት ያሉት ሂደቶችን የሚከታተሉ ኮሚቴ በመምረጥ የጁፒተር ሆቴል መርሐግብር ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ