የነገውን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።
በተዋጣለት ሁኔታ አዳማ ከተማን ማሸነፍ የቻለው ወላይታ ድቻ በጨዋታው ያሳየው አቋም ቀጣይነት ያለው መሆኑን ለማሳየት የነገውን ፈተና መወጣት ይኖርበታል። በእርግጥ ወልቂጤ ከተማም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በነበረው ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ይቅር እንጂ ያለቀላቸውን የግብ ዕድሎች በመፍጠሩ በኩል ጥሩ ጨዋታ አሳልፎ ነበር። በሁለቱ ቡድኖች የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ከታየው የአማካይ ክፍላቸው መልካም እንቅስቃሴ አንፃርም የነገው ጨዋታ የመሀል ሜዳ ፍልሚያው የሚጠበቅ ይሆናል።
ወደ መሀል የጠበበው የወልቂጤ ከተማ የማጥቃት ሂደት ፊት መስመር ላይ ጨራሽ አጥቂ ከማጣት ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ብቻ ሳይሆን የሜዳውን ስፋት በአግባቡ በመጠቀም ረገድ በነገው ጨዋታ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። ለዚህም ቡድኑ የያዘው ስብስብ የጥራት ደረጃ የሚታማ ባለመሆኑ ለአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጥሩ አማራጭ የሚሰጥ ይሆናል። ከዚህም በላይ ግን ቡድኑ የፊት መስመሩን ስልነት ይበልጥ ማስተካከል ይኖርበታል። በጨዋታ መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የማጥቃት ኃይል የሚታይበት ወላይታ ድቻ ባደረጋቸው ሁለቱም ጨዋታዎች በቶሎ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ግን የበላይነቱን እስከመጨረሻው የማስቀጠል እና ጨዋታን አቀዝቅዞ የመጨረስ ጠንካራ ጎን ታይቶበታል። እንደቀድሞው እየቀነሰ የሚሄድ ጉልበት የሚታይበት ከሆነ ግን እስከጨዋታ ፍፃሜ መፋለም እንደሙችል በቡናው ጨዋታ ባሳየው በወልቂጤ የበላይነት ሊወሰድበት የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
የወልቂጤው የግራ መስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ በቦታው በቡድኑ ብቻ ሳይሆን በሊጉም ካሉ ጥሩ ተጫዋቾች አንዱ እንደመሆኑ በነገው ጨዋታ የሚኖረው እንቅስቃሴ ይጠበቃል። በድቻ በኩልም መሀል ሜዳ ላይ ድንቅ ጥምረት ያሳዩት ኤልያስ አህመድ እና እንድሪስ ሰዒድ እንዲሁም አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ በቡድናቸው የማጥቃት ሂደት ላይ የሙኖራቸው ሚና ተጠባቂ ይሆናል።
አናጋው ባደግን በቅጣት የሚያጣው ወላይታ ድቻ ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ፍኒያንስ ተመስገን ፣ ያሬድ ዳንሳ እና እዮብ ዓለማየሁ ከጉዳት ያላገገሙለት ሲሆን አብነት ደምሴ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ይሆናል። የተጫዋቾቹን የኮቪድ ውጤት ነገ የሚያውቀው ወልቂጤ ከተማ ከተማ ደግሞ ግብ ጠባቂዎቹ ጀማል ጣሰው እና ጆርጅ ደስታ በጉዳት ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን አዳነ በላይነህም ወደ ሜዳ አይመለስም። በጅማው ጨዋታ ቀላል ጉዳት ገጥሞት የነበረው ሙኸጅር መኪ ግን ለጨዋታው ይደርሳል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት ሁላቱ ቡድኖች በተሰረዘው የውድድር ዓመት በተገናኙበት ወቅት ወልቂጤ ከተማ በቀድሞው አጥቂው ጫላ ተሺታ ጎል 1-0 አሸንፎ ነበር።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)
ሰዒድ ሀብታሙ
ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – መሳይ አገኘሁ
በረከት ወልዴ
ፀጋዬ ብርሀኑ – ኤልያስ አህመድ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ
ስንታየሁ መንግሥቱ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ዮሃንስ በዛብህ
ሥዩም ተስፋዬ – አሚኑ ነስሩ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ
ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ
አሜ መሐመድ – ሄኖክ አየለ – ያሬድ ታደሰ
© ሶከር ኢትዮጵያ