ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ጅማን በመርታት ወደ ድል ተመልሷል

በሦስተኛው ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማ ጅማ አባ ጅፋርን 4-1 ማሸነፍ ችሏል።

ጅማ አባ ጅፋር ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ ትርታዬ ደመቀን በሀብታሙ ንጉሴ ፣ አብርሀም ታምራትን በሳዲቅ ሴቾ ፣ ተመስገን ደረሰን በብዙዓየሁ እንዳሻው በመተካት ጨዋታውን ሲጀምር ፋሲል ከነማ ደግሞ በቡናው ጨዋታ ከተጠቀመው ስብስብ ውስጥ በሰዒድ ሀሰን ፣ በዛብህ መለዮ እና በረከት ደስታ ቦታ እንየው ካሳሁን ፣ አምሳሉ ጥላሁን እና ይሁን እንዳሻውን ተጠቅሟል።

ሙሉ ለሙሉ የፋሲል ከነማ ብልጫ የተስተዋለበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። ከቆሙ ኳሶች እና ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች የግንባር ሙከራዎች እንዲሁም ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ፋሲሎች የኳስ ቁጥጥሩን በእጃቸው ቢያደርጉም ያለቀላቸው ዕድሎችን ግን ወዲያው መፍጠር አልጀመሩም። 27ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ከሱራፌል ዳኛቸው የተሻማለትን ኳስ በግንባር ሲሞክር እንዲሁም ያሬድ ባየህ 32ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ኳስ ወደ ጎል ሲልክ ነበር የጅማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ግብ የማዳን ኃላፊነቱ የተፈተሸው።

ጅማዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው በመከላከል ሊደረግባቸው የሚሉትን አደገኛ ሙከራዎች መቆጣጠር የቻሉት ግን እስከ 38ኛው ደቂቃ ነበር። ሽመክት ጉግሳ ከተከላካዮች አምልጦ ከሱራፌል የተላከለትን ኳስ ይዞ ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክር በወንድምአገኝ ማርቆስ ጥፋት ተሰርቶበት የተሰጠውን ቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን በድንቅ ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም እንዲሁ ሽመክት ከቀኝ መስመር ከሳሙኤል ዮሃንስ ወደ ፊት የተላከውን ኳስ ተከትሎ ከፔንዜ ጋር ከተገናኘ በኋላ ለሙጂብ ቃሲም አሳልፎለት ሙጂብ የፋሲልን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ጅማዎች በተሻለ ሁኔታ በፋሲል ሜዳ ላይ መታየት ሲጀምሩ ሱራፌል ዐወል እና ብዙአየሁ እንዳሻው ከሳጥን ውጪ ሙከራዎች አድርጋዋል። ቀስ በቀስ ግን የጨዋታ ሂደቱ ወደነበረበት ተመልሶ ጅማዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገዋል። ሙጂብ ቃሲም ከሽመክት እና ከሳሙኤል ዮሀንስ በተቀበላቸውን ኳሶች ከባድ የማይባሉ ሙከራዎችን ያደረጉት ፋሲሎች 66ኛው ደቂቃ ላይ በይሁን እንዳሻው የሳጥን ጠርዝ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሆኖም ረጃጅም ካሶችን በመላክ ዕድል ለመፍጠር ይሞክሩ የነበሩት ጅማዎች በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ያሻሙት ኳስ የሚኬል ሳማኬ ስህተት ታክሎበት በብዙአየሁ እንዳሻው ወደ ግብነት ተቀይሯል።

ጅማዎች ልዩነቱን ማጥበብ የቻሉት ግን ለአምስት ደቂቃ ብቻ ነበር። ፋሲሎች በጅማዎች ግብ አቅራቢያ ያቋረጡትን ኳስ ሽመክት አመቻችቶለት ሳሙኤል ዮሀንስ ሦስተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። 88ኛው ደቂቃ ላይም የዕለቱ ኮከብ የነበረው ሽመክት ጉግሳ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን እና በሱራፌል ምትክ ከገባው በረከት ደስታ ጋር የተቀባበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ ፋሲል ከነማ ያለብዙ ችግር ተጋጣሚውን 4-1 እንዲያሸንፍ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ