ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል

ረፋድ ላይ በተከናወነው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን 2-0 አሸንፏል።

ባህር ዳር ከተማ በሀዲያ ሆሳዕና ከተሸነፈበት ጨዋታ ሣላአምላክ ተገኝን በአህመድ ረሺድ እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙን በግርማ ዲሳሳ ተክቷል። በድቻ ሽንፈት ሲገጥማቸው ከጀመሩበት ቡድን በተመሳሳይ ሁለት ለውጦች ያዳረጉት አዳማዎችም ጀሚል ያዕቆብ እና በላይ አባይነህን በፍሰሀ ቶማስ እና አክሊሉ ተፈራ ቦታ ተጠቅመዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚዎቹ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ የሚያመላክት ነበር። ገና በ4ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ከሳጥኑ መግቢያ አካባቢ ፍፁም ዓለሙ በቀጥታ በመምታት አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላ በነበሩት አብዛኛዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ኢላማቸውን የጠበቁ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲያደርጉ አዳማዋች የግብ ክልላቸውን በቅጡ መከላከል ተስኗቸው ታይተዋል። 10 እና 13 ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ የፈጠራቸው የመጨረሻ የግብ ዕድሎች ፍፁም ዓለሙ እና ግርማ ዲሳሳ ሞክረዋቸው በታሪክ ጌትነት ድነዋል። ግርማ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከፍፁም ሌላ ኳስ ተቀብሎ ያደረገውም ሙከራ በታሪክ ጥረት ነበር የወጣው።

20ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ካደረገው ሌላ ጠንካራ የግብ ሙከራ በኋላ አዳማዎች ተጋጣሚያቸው ከኳስ ጋር ወደ ሳጥናቸው በተደጋጋሚ ይገባ የነበረበትን ሂደት ቢቀንሱሙ አብዛኛውን ደቂቃ ከኳስ ቁጥጥር ውጪ ነበሩ። ከ37ኛው ደቂቃ የየኋላሸት ፍቃዱ ቀለል ያለ እና ሀሪሰን ሄሱ በቀላሉ ከያዘው ሙከራ ውጪም ሌላ የግብ ዕድል አልፈጠሩም። በአንፃሩ ጨዋታው ቀሏቸው የታዩት ባህር ዳሮች አልፎ አልፎ ቀጥተኛ ኳሶችን በመጣል አደጋ ለመፍጠር ሲሞክሩ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱንም አልለቀቁም። 35ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ ከግራ መስመር በላከው እና ባዬ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብም መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በእንቅስቃሴ ዝግ ያለ እና በርከት ያሉ ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሀሳባቸውን ማጥቃት ላይ አድርገው የገቡት አዳማዎች ባሰቡት መንገድ የውጤት ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። 58ኛው ደቂቃ ላይ ከጀሚል ያዕቆብ ማዕዘን ምት ታፈሰ ሰራካ በግንባር ያደረገው ቀላል ሙከራ በኋላ 77ኛው ደቂቃ ላይ በቃሉ ገነነ የቡድኑን ከባድ ሙከራ ከርቀት ቢያደርግም ሀሪስተን ሄሱ አድኖበታል። ጨዋታውን የጀመሩበትን ፍጥነት ቀንሰው ተጋጣሚያቸውን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ያደረጉት ባህር ዳሮች አልፎ አልፎ በቀጥተኛ ኳሶች ወደ ግብ ቢደርሱም እንደመጀመሪያው አስፈሪ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልታዩም። ያም ቢሆን መሪነታቸውን አስጠብቀው በመጨረስ የኃይል አጨዋወት እየተንፀባረቀበት የመጣውን ጨዋታ አሸንፈው መውጣት ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ