የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 1-4 ፋሲል ከነማ

አምስት ግቦች ከተስተናገዱበት የፋሲል ከነማ እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ያሰቡትን ነገር በጨዋታው ስለማግኘታቸው…

ተጫዋቾቼ የነበራቸው የማሸነፍ ስሜት በጣም ደስ የሚል ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ግብ አካባቢ የመቻኮል ነገር ይታያል። ከጨዋታ ጨዋታ ማደግ ይኖርብናል። በዛሬው ጨዋታ በሰፊ ጎል ማሸነፋችን ግን ለቀጣይ ጉዟችን ጥሩ ነው። ሥነ-ልቦናችንን ከፍ ያደርግልናል።

ሽመክት ጉግሳ በሜዳ ላይ ስላሳየው ብቃት…

ሽመክት ጥሩ ነበር። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ተሳትፎ ድንቅ ነበር። በጨዋታው የነበረውም ፍላጎት ትልቅ ነበር። እርግጥ እርሱ ጨዋታ ላይ ብቻ ሳይሆን ልምምድ ላይም እንደዚሁ ነው። ከዚህም በላይ መሻሻል ስለሚችል ግን አሁንም መጠንከር አለበት።

ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባጅፋር

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉብን ያሳያል። ካለው ነባራዊ ሁኔታ እና ችግር ጋር ሆነንም ቢሆን መስራት ያለብንን ነገሮች እንዳሉ አይተናል። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ለእኔ ጥሩም ሆነ መጥፎ አደለም። ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩን ግን ያስታወቀ ነው።

ስለ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞ…

የሚያግዘኝ አካል ካለ ብሩህ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ። ዓምናም እንደምታቁት በውጥንቅጦች ውስጥ ነበር የሰራሁት። እንደዛም ሆኖ ውጤታችን መጥፎ አልነበረም። ትላልቅ ቡድኖችን ነጥብ እናስጥል ነበር። ዘንድሮ ግን እንደ ዓምናው ሰፊ የዝግጅት ጊዜም አልነበረንም። እኔ ግን መናገር የምፈልገው አቅሜ እስከፈቀደው ድረስ የምችለውን እንደምሰራ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ