የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-0 አዳማ ከተማ

ከዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከሁለቱ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርጋለች።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው…

“በመጀመሪያው አጋማሽ በምንፈልገው መንገድ ተጫውተናል ፤ የምፈልጋቸውን ጎሎችም አግኝተናል። መጠቀም አልቻልንም እንጂ ሌሎችም የግብ ዕድሎችም ፈጥረናል ፤ በእሱ ደስተኛ አይደለሁም። በዛ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከሚገባው በላይ ፍጥነት በመጠቀማችን ሁለተኛው አጋማሽ በተጫዋቾቼ ላይ መውረድ ነበር። እንደዛም ሆኖ ኳሶችን ከመሳታችን ውጪ ጨዋታውን ተቆጣጥረን መጨረስ ችለናል።”

ስለሁለተኛው አጋማሽ የቡድኑ መቀዛቀዝ…

“በሁለት ዓይነት መንገድ ነው። የመጀመሪያው ትንሽ ፍጥነታችንን ቀንሰን የተጋጣሚያችንን ክፍተት ለመፈለግ በማሰብ ነው። በዛው ልክ ሁለት ጎል ከማግባታችን አንፃር በጣም ተጨንቀን ቶሎ ቶሎ የግብ ዕድል ለመፈለግ ዕድሉ የለንም። ምክንያቱም ከሁለት ከሦስት ቀን በኋላ ወሳኝ የሆኑ ጨዋታዎች ስላሉንን ተጫዋቾቻችንን መጠበቅ አለብን። በዛው ልክ ደግሞ የባለፈውም የዛሬውም ጨዋታ ግጭት የበዛበት ነበር። ተጫዋቾች ከሚገባው በላይ ጉልበት እየተጠቀሙ ነው። የመሸነፍ እና የማሸነፍ ጉዳይ አይደለም። እዚህ ውስጥ ተጫዋቾቻንን እንዳናጣ በጣም እፈራለሁ እና ዳኝነቱም ትኩረት ቢደረግበት ለማለት እፈልጋለሁ።”

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው…

” በመጀመሪያ ደቂቃዎች የሚቆጠሩ ጎሎች ጫና ውስጥ እየከተቱን ነው ፤ በሁለቱም ጨዋታ። ይሄን አሻሽለን ለመቅረብ እንሞክራለን። በተረፈ በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል ፤ ሙከራም አድርገናል። የተመጣጠነ ነበር ከእረፍት በኋላ የነበረው ጨዋታ። በቶሎ ግብ ማስተናገዳችን ግን ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ነበረው።”

ስለፊት መስመሩ ድክመት…

“ያው ጉዳት አለብን። ያልገቡ ሁለት ሦስት ተጫዋቾች አሉ። አብዲሳም ዋና አጥቂያችን ነው ፤ ጉዳት ላይ ነው። ስንመጣም ከአዳማ ጀምሮ ጉዳት ላይ ያለ ተጫዋች ነው። ባለፈውም ቀይረን አስገብተነው ጉዳቱ በዛበት። በተረፈ ውድድሩ ገና ነው። ጠንክረን ለመቅረብ እንሞክራለን። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ