“በእኛ መሐል ምንም የተፈጠረ ቅራኔ የለም” – ሽመክት ጉግሳ

ከሽንፈት መልስ ጅማ አባ ጅፋር በመርታት ቡድኑ ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ በማስቻል የዛሬ ጨዋታ ኮከብ ከነበረው ሽመክት ጉግሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከፋሲል ከነማ ስኬት ጀርባ ይህ ድንቅ የመስመር አጥቂ ይገኛል። በተለይ ሙጂብ ቃሲም ጎል ማስቆጠር እና በሱራፌል ዳኛቸው ምርጥ አቋም ውስጥ ይህ ጠንካራ ተጫዋች ይገኛል። በማጥቃት በመከላከሉ ረገድ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን ሲያስመሰክር የቆየው ሽመልስ ጉግሳ በዛሬው ዕለት ጅማ አባ ጅፋርን በሰፊ የጎል ልዮነት ዐፄዎቹ ሲረቱ አንድ ጎል ከማግባቱም ባሻገር ለሦስቱም ጎሎች መቆጠር የእርሱ ሚና የላቀ ነበር። የዛሬው ጨዋታ ኮከብ ሆኖ ከዋለው ሽመልስ ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አግኝተን አውርተነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” የዛሬው ጨዋታ በጣም አሪፍ ነበር። ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር። በዚህም የተሻለ ውጤት አስመዝግበናል። ማሸነፋችን ይገባን ነበር። ቡድናችን ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ነው። እኔም ዘንድሮ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ ነው የተነሳሁት። ምክንያቱም ይህ የዘንድሮ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተላለፍ ጨዋታ ነው። ስለዚህ ለዚህ ውድድር የሚመጥን ዝግጅት ሳደርግ ነው የቆየሁት። አሁን ባለኝ አጀማመር ደስተኛ ነኝ። ይሄንንም ወደፊት አስጠብቃለው።

“ቡድናችን ውስጥ አለመስማማት እንዳለ ይነገራል። ግን በመካከላችን ጥሩ ፍቅር መከባበር አለ። በአጋጣሚ የሆነ ሰዓት ከሽንፈቱ በኃላ አንድ ነገር ተከስቶ ነበር። አሁን በእኛ መሐል ምንም የተፈጠረ ቅራኔ የለም። ቡድናችን ለዋንጫ ነው የሚጫወተው አንዳንዴ ለዋንጫ ስትጫወት እንዲህ ያለ ነገር ሊፈጠር ይችላል። ከዚህ በኋላ የምንነሳበት መንገድ ነው። ሁሉን ነገር ረስተን በአሸናፊነት መንፈስ መቀጠል አለብን። በዚህ መንፈስ ካልቀጠልን ልንቸገር እንችላለን። ስለዚህ ደጋፊዎቻችን የሚፈልጉትን ዋንጫ ለማንሳት እንደ ቡድን በአንድ መንፈስ በመሆን ጠንክረን እንሰራለን።”

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስለ ሽመክት ጉግሳ ይህን ተናግረዋል።

“ሽመክት ጥሩ ነበር። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ተሳትፎ ድንቅ ነበር። በጨዋታው የነበረውም ፍላጎት ትልቅ ነበር። እርግጥ እርሱ ጨዋታ ላይ ብቻ ሳይሆን ልምምድ ላይም እንደዚሁ ነው። ከዚህም በላይ መሻሻል ስለሚችል ግን አሁንም መጠንከር አለበት።”


© ሶከር ኢትዮጵያ