የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-2 ወልቂጤ ከተማ

የሦስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ መርሐ-ግብር የሆነው የወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ትንሽ ጠንከር ያለ ጨዋታ ነበር። እነሱ ከማሸነፍ ነበር የመጡት፣ እኛ ደግሞ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በዚህም በጫና ውስጥ ሆነን ነበር ጨዋታውን የጀመርነው። በጨዋታውም ያሰብነውን ሁሉ በሜዳ ላይ አድርገናል ብዬ ባልናገርም ተጫዋቾቼ በሜዳ ላይ ተጋድሎ አድርገው ያስመዘገቡት ሦስት ነጥብ እጅግ የሚያስደስት ነው።

ተጫዋቾቹ ስላደረጉት እንቅስቃሴ…

ሁሉም ቦታ ላይ ያሰለፍናቸው ተጫዋቾች የሚችሉትን ሁሉ በሜዳ ላይ አድርገዋል። የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በደንብ እንዲገቡ እና የቁጥር ብልጫ እንድንወስድ አስበን ነበር። ይህም ሀሳባችን ተሳክቶልን የተገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ቀይረናል። ሆኖም ግን ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን በፈለግነው መንገድ አልነበረም የከወነው። ሁለት ጎሎችን ካገባን በኋላም ሌሎች ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ነገር ግን አልተጠቀምንበትም። የያዝነውን ኳስም የመልቀቅ ነገር ይታይብን ነበር። በተለይ በመጨረሻዎች ደቂቃዎች ረጃጅም ኳሶችን እንጠቀም ነበር። ይህንን ጭራሽ አስበነው አልነበረም። ውጤቱን ከማስጠበቅ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ወደፊት ግን ይህንን አስተካክለን እንቀርባለን።

ደለለኝ ደቻሳ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው…

እኔ ጨዋታውን ለሁለት ከፍዬ ነው የማየው። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ኳሱን ይዘን ለመጫወት ስንሞክር ወልቂጤዎች ተጭነውን ሲጫወቱ ነበር። ከዚህም የተነሳ ወደ ሌላ አጨዋወት በመሄድ በረጃጅም ኳሶች ለመውጣት ሞክረናል። ግን በመከላከል ስህተት የመጀመሪያው ጎል ገባብን። በሁለተኛው አጋማሽም የተወሰነ ለውጥ አድርገን ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ ሞክረናል። በዚህ እንቅስቃሴም ጎል አስቆጥረናል። ግን ከሽንፈት የታደገን ጎል አልነበረም።


© ሶከር ኢትዮጵያ