ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ያለ ግብ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር የተቀዛቀዘ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል፡፡
ብዙም ለዕይታ ሳቢ ባልሆነው እና በተናጥል ግን በግል ተጫዋቾች ነጥረው የወጡበት ጨዋታ ነበር፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች አብዛኛዎቹን የማጥቃት ሒደት በግራ በኩል ባዘነበለው የመሳይ ተመስገን ቦታ ኳስን ሲያገኙ በተጫዋቿ አቅም ሰብሮ ለመግባት በሚደረግ ጥረት ጫናዎች ለማሳደር የጣሩ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች በተወሰነ መልኩ አልፎ አልፎ በሚገኙ አጋጣሚዎች ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም የጠጠረውን የሀዋሳን የተከላካይ በቀላሉ መሻገር ግን ተስኗቸው ታይቷል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች በዓይናለም አሳምነው አማካኝነት ያለቀለትን የማግባት ዕድል ቢያገኙም ተጫዋቿ በቀላሉ አምክናዋለች፡፡ በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማ በመሳይ ተመስገን አማካኝነት ተጨማሪ ሁለት ሙከራን አድርገው ቤቴልሄም ዮሀንስ ተቆጣጥራዋለች፡፡26ኛው ደቂቃ የሀዋሳ ግብ ጠባቂ አባይነሽ ኤርቄሎ ለቡድን አጋሯ ቅድስት ዘለቀ ያቀበለችውን ኳስ በድጋሚ ቅድስት መልሼ ለዓባይነሽ እሰጣለሁ ብላ አቅጣጫዋን ቀይራ አዲስ አበባዎች መሪ ታደርግ የነበረችሁ ኳስ ወጥታለች፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ከተማዎች ያገኙት የስህተት ኳስ መስታወት አወቀ አግኝታ ሳትጠቀምቀት ቀርታለች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ሒደት ከተከላካይ መስመሩ ላይ ተጫዋች በመቀነስ አጥቂዋን ረድኤት አስረሳኸኝን በማስገባት ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል፡፡ ሆኖም ኳስን ከመረብ ጋር ለማገናኘት የአዲስ አበባዋን ግብ ጠባቂ ቤቴልሄምን ማለፍ ግን ተስተኗቸዋል፡፡በተለይ በተደጋጋሚ በመሳይ ተመስገን እና ረድኤት አስረሳኸ ግብ ለማስቆጠር ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂዋ ቤቴልሄም ዮሀንስ እና የቡድኑ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ አንድ ነጥብ ፍለጋ ሜዳ ላይ በመውደቅ ከሀዋሳ ላይ አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል፡፡ ጨዋታውም ምንም ግብ ሳይስተናገድበት 0ለ0 ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአዲስ አበባ ከተማዋን ግብ ጠባቂ ቤቴልሄም ዮሐንስን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡

– በሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሁንም በርካታ ተጫዋቾች የኮቪድ 19 ቫይረስ እየተገኘባቸው ሲሆን ከሁለቱ ክለብ በድምሩ አምስቱ የዚህ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሀዋሳው ከተማው የህክምና ባለሙያ ዘሪሁን ዳዊት ይህንን በሽታ ለመቀነስ በግሉ የሜዳውን ወሳኝ ቦታዎች በፀረ ተዋህሲያን መርጫ በመርጨት ሲያደርግ የነበረበት አጋጣሚ የሚበረታታ መልካም ተግባር ነው፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ