ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በሦስተኛው ሳምንት የመጨረሻ ዕለት ቀዳሚ ጨዋታ ላይ እነዚህን ነጥቦች አንስተናል።

ሊጉን በድል እና በመልካም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጀምረው በሁለተኛው ሳምንት የተገላቢጦሽ የሆነባቸው ባህር ዳር እና አዳማ ወደ አጀማመራቸው ለመመለስ እርስ በእርስ ይፋለማሉ።

ባህር ዳሮች ሲዳማን ሲያሸንፉ የነበራቸው የቡድን እና የግል ብቃት በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ላይ ተዳክሞ ታይቷል። ቡድኑ ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር በፍጥነት ግብ ላይ ይደርስ የነበረበት መንገድ እና የፊተኛው የቡድኑ ክፍል ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ትጋት ቀጣይነት ያለው እንጂ በቶሎ የሚከስም አይመስልም ነበር። በነገው ጨዋታም በቶሎ ወደጠንካራ መንፈሱ ካልተመለሰ መቸገሩ የሚቀር አይመስልም። በተለይም ከኃላ የተደራጀ የተከላካይ ክፍል ሲገጥመው እና መሀል ሜዳ ላይም ተጋጣሚው ኃይል ላይ ያመዘነ እንዲሁም ቁልፍ ተጫዋቾቹ ላይ ትኩረት ያደረገ አጨዋወትን ሲተገብር የታየበት ቀስ በቀስ ከማጥቃት መንፈስ የመንሸራተት ችግር ሊፈትነው ይችላል። ይህ ጉዳይ እንደተጋጣሚው የጨዋታ አመራረጥ የሚወሰን ቢሆንም ቡድኑ በመሰል ሁኔታዎች ውስጥ ማምለጫ የሚሆን ሁለተኛ ዕቅድ እንደሚያስፈልገው ግን የሚያመላክት ነበር። ነገ ግን ኳስ ይዞ የሚጫወት ፣ በማጥቃት ሂደቱ ላይም በዋነኝነት ሦስቱን የማጥቃት አማካዮቹን እና የመስመር ተከላካዮቹን የሚጠቀም ባህር ዳር በጨዋታው ይጠበቃል።

በተመሳሳይ ጅማን ሲረታ የተዋጣለት ሊባል የሚችል እንቅስቃሴን አሳይቶ የነበረው አዳማ ጠንካራ ጎኖቹን አጥቶ መታየቱ የነገው ጨዋታ ላይ የሚኖረው መልክ ከወዲሁ እንዲጠበቅ አድርጎታል። በተለይም ከተከላካይ መስመር ጀርባ የሚኖረውን ክፍተት በቶሎ መሸፈን ላይ የታየበት ክፍተት ለባህር ዳር ፈጣን አጥቂዎች አሳልፎ እንዳይሰጠው ያሰጋዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ኳስ በሚፈልግበት እና ትኩረቱ በአመዛኙ ማጥቃት ላይ በሚሆንበት ወቅት በቶሎ ኳስ ለመንጠቅ በብዙ የሚቸገር መሆኑ እንደነገ ተጋጣሚው ዓይነት ለኳስ ቁጥጥር ፍላጎት ያለው ቡድን ሲገጥመው የሚያሰጋው ነጥብ ነው። ከዚህ ውጪ አዳማ ፊት መስመር ላይ የዳዋ ሆቴሳን ቦታ በአግባቡ መተካቱን በሚያጠራጥር መልኩ ስልነት ጎድሎት ታይቷል። ይህንን ለማስተካከልም በቡድኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። እነዚህ ነጥቦች ሲታዩ ምንም እንኳን በሁለተኛው ሳምንት ሁለቱም ሽንፈትን ቢቀምሱም እስከመጨረሻው ድረስ ታግሎ የተሸነፈው ባህርዳር ያለበት ክፍተቶች ከአዳማ አንፃር ሲታዩ የተሻሉ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳሉ።

በጨዋታው የባህር ዳሩ አማካይ አፈወርቅ ኃይሉ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ፍፁም ዓለሙ ግን በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል። በአዳማ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተው እና ቀለል ያለ ልምምድ የጀመረው ሱለይማን መሀመድ ፣ ሙሉ ጤና ላይ ያልነበረው አብዲሳ ጀማል እና ፍሰሀ ቶማስ በጉዳት ለነገው ጨዋታ እንደማይደርሱ ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2011 የውድድር ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያውን ጨዋታ ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ሁለተኛውን ባህር ዳር ከተማ አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪሰን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ዜናው ፈረደ – ፍፁም ዓለሙ – ምንይሉ ወንድሙ

ባዬ ገዛኸኝ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ታሪክ ጌትነት

ታፈሰ ሰረካ – ደስታ ጌቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ

ዘሪሁን ብርሀኑ – ደሳለኝ ደባሽ

ፀጋዬ ባልቻ – በቃሉ ገነነ – ጀሚል ያዕቆብ

የኋላእሸት ፍቃዱ


© ሶከር ኢትዮጵያ