ከፍተኛ ሊግ | ሀምበሪቾ ዱራሜ ወሳኝ ዝውውሮችን ፈፅሟል

ሀምበሪቾ ዱራሜ በፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸው እና የውጪ ዜጎችን ጨምሮ አስር አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሟል፡፡

ግርማ ታደሰን በአሰልጣኝነት ቀጥሮ በዱራሜ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ሀምበሪቾ ዱራሜ ከዚህ ቀደም ስድስት ተጫዋቾች አስፈርሞ የነበረ ሲሆን በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ይረዳው ዘንድ አስር የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

አዳማ ሲሶኮ ከተቀላቀሉት መካከል ነው። በ2010 ጅማን ተቀላቅሎ ከክለቡ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ማሊያዊው ተከላካይ ዓምን በባህር ዳር ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ዘንድሮ ወደ መቐለ ቢያመራም በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሀምበሪቾ አምርቷል።

የናይጄሪያ ዜግነት ያለው አንጋፋው የቀድሞ የስሑል ሽረ ግብ ጠባቂ ሰንድይ ሮቲሚ የዱራሜውን ክለብ የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ሲሆን በሀገሩ ናይጄሪያ ዲያፋ አካዳሚ ውስጥ ሲጫወት የቆየው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቻርለስ ሪባኑ እና ጋናዊው የቀድሞ የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ አትራም ኩዋሜ ሌሎቹ የውጪ ዜጎች ናቸው።

ሀምበሪቾዎች ከውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ባሻገር የቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ጊዜ የነበረውን ፈጣኑን የመስመር አጥቂ ራምኬል ሎክንም በእጁ አስገብቷል። ምስጋናው ወልደ ዮሀንስ (ተከላካይ) ከወልዋሎ አዲግራት፣ አቤኔዘር ኦቴ (ተከላካይ) ከወልቂጤ ከተማ፣ ዋቁማ ዲንሳ (አማካይ) ከነቀምት ከተማ፣ ወጣቱ አጥቂ ታምራት ስላስ ከወላይታ ድቻ እና በጅማ አባጅፋር አምና ሊጉ እስኪሰረዝ ድረስ ጥሩ ጊዜ የነበረው አጥቂው አምረላ ደልታታ ለክለቡ የፈረሙ አዳዲስ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ