በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 4:00 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከተማን በሚገባ ተፈትኖ 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ቅርፅ የሌለው እና ግብ ለማስቆጠር ቡድኖቹ ያላቸው ፍላጎትም እጅጉን የወረደ ነበር፡፡ ኤሌክትሪኮች እፀገነት ብዙነህን ከተከላካይ ስፍራ ወደ መሐል አምጠው ማጫወታቸው ለሰሚራ ከማል እንቅስቃሴ መሸፈን እና በአግባቡም ለአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ኳስን ለማድረግ በሚገባ ሲቸገሩ ያየንበት ነበር፡፡ አርባምንጮች በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን በኳሶቹ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጥ ተጫዋች ባለመኖሩ በተደጋጋሚ ለመክኑ ችለዋል፡፡በዚህኛው አጋማሽ ፋሲካ በቀለ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባር ገጭታ የግቡ ቋሚ የጨረፈበት አጋጣሚ በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል የታየች ብቸኛ ሙከራ ነበረች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኖቹ መጠነኛ መሻሻልን በእንቅስቃሴ ደረጃ ማሳየት ቢችሉም ወደ ግብ ደርሶ ጎል ለማስቆጠር ያላቸው አፈፃፀም ግን እጅጉን ደካማ ነበር፡፡ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ቡድን በእንቅስቃሴ የተሻለ ቢሆንም በግብ ሙከራ እና በፍላጎት ለመጫወት የአርባምንጭ ያህል አልነበረም፡፡ 66ኛው ደቂቃ ወርቄ ዛቶ በጥሩ ቅብብል የተገኘን አጋጣሚ ተቀይራ ለገባችው ቤተል ጥላ ሰጥታት አጥቂዋም ከግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ ጋር ተገናኝታ በቀላሉ ያመከነቻት ኳስ እጅጉን አርባምንጮችን ዋጋ ያስከፈለች ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ስንዱ ዳምጠው ወደ ግራ ባደላ ቦታ ቅጣት ምት አግኝታ በቀጥታ ወደ ጎል ማታ የግቡ ቋሚ የላይኛው ዘንግ የመለሰባት ሌላኛው የአርባምንጭ መልካም ዕድል ነበረች፡፡
የብስለት እና የአጨራረስ ክፍተት የታየባቸው አርባምንጭ ከተማዎች በመከላከል ሂደቱ ላይ የሰሩትን ስህተት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሚገባ በመጠቀም 75ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥራለች፡፡ ተቀይራ የገባችሁ ጤናዬ ወመሴ በግራ የአርባምንጭ የግብ ክልል ወደ ሳጥን የላከችሁን ኳስ ፋና ዘነበ ወደ ግብነት ለውጣው ኤሌክትሪክን አሸናፊ በማድረግ ጨዋታው 1ለ0 ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ግብ አስቆጣሪዋን ልደት ቶሎአን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ