ሲዳማ ቡና ክስ መስርቷል

ዛሬ በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት የገጠመው ሲዳማ ‘ተጫዋቾቼን እንዳልጠቀም ተደርጊያለሁ’ ሲል የክስ ሪዘርቭ አስይዟል።

ዛሬ በሁለተኛ የሊጉ ጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕናን ገጥሞ 3-1 የተሸነፈው ሲዳማ ቡና ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ነበር ወደ ሜዳ የገባው። በአንፃሩ ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና አምስት የውጪ ዜጎችን አሰልፎ ተሰላፊዎቹም በጨዋታው ላይ በጎ ተፅዕኗቸውን አሳይተው በድኑን ለድል ሲያበቁ ተስተውሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከቡድኖቹ አሰልጣኞች ጋር በነበረን ቆይታም የሲዳማው አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ “የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ ሳይጨርሱ አይጫወቱም ተብሎ ዛሬ አራት ሰዓት ላይ ነው ከአሰላለፍ ያወጣናቸው” ያሏቸውን የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች እንዳይጠቀሙ መደረጋቸውን ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በጉዳዩ ዙሪያ ክስ ማስያዛቸውን በተከታዩ አስተያየታቸው ገልፀዋል።

“ቡድን ሰርተን ጨርሰን ነበር። የቀሩብን ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው። የሀዲያ ሆሳዕና የውጪ ዜጎች ግን እየተጫወቱ ነው። ጉዳያችን ተመሳሳይ ነው። ሲስተሙም የቆመው ለሁሉም ቡድን ነው። የእኛን ብቻ ማስቆም ለምን እንዳስፈለገ አላውቅም። በክለባችን ፕሬዝዳንት በኩል ማጫወት እንደማንችል ነው የሰማነው። ለዚህም ክስ ሪዘርቭ አስይዘናል ፌዴሬሽኑ የሚወስነውን እናያለን። ችግሩ በጨዋታው ተፅዕኖ ፈጥሮብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ