በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ በርካቶችን ያዝናናው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በባንክ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በሴቶች ፕሪምየር ሊግ እስከ አሁን ከታዩ ጨዋታዎች ለየት ያለ ጠንካራ ፉክክርን ያስተናገደው የድሬዳዋ ከተማ እና የንግድ ባንክ የ10:00 ጨዋታ የተጠና እንዲሁም በሳል የሆነ እንቅሴቃሴ በሁለቱም በኩል ታይቶበታል፡፡ በተለይ የሁለቱ ቡድኖች የመሀል ሜዳ ክፍል ሲያሳይ የነበረው ፈጣን ሽግግር ለዕይታ ማራኪ እንዲሆን ያስቻለ ነበር፡፡ በንግድ ባንክ በኩል ህይወት ደንጊሶ ለቡድኑ የመከላከልም ሆነ የማጥቃት ሀይል ኳስን በማደራጀት ለቡድኑ ጓደኞቿ ስትልክ የነበረበት መንገድ እጅጉን አስገራሚ ነበር፡፡ተጫዋቿ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ሁለት ኳሶችን ከርቀት አግኝታ የሞከረችበት አጋጣሚ ሊጠቀስ የሚችል ግሩም ሙከራዎች ነበሩ፡፡
በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በተመሳሳይ በመሀል ክፍሉ ላይ ማዕድን ሳህሉ እና ማዕከል በማድረግ ወደ አጥቂዋ ቁምነገር ካሳ በማሻገር የባንክን የተከላካይ ክፍል ለመረበሽ ችለዋል፡፡ በዚህም ሂደት ግብ አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ ተብለዋል፡፡ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣላቸው የነበሩት ድሬዳዋዎች ኳስን ይዘው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም የኳሱ የመጨረሻ ማረፊያ የተሳካ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡
ንግድ ባንኮችን በተደራጀ የቅብብል መንገድ 20ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ደርሰው ብርቱካን ገብረክርስቶስ አግኝታ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ በቀላሉ ሳትጠቀምቀት ቀርታለች፡፡ወደ መልበሻ ክፍሉ ሊያመሩ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው ህይወት ደንጊሶ ከቅጣት ምት አደገኛ ኳስ መታ ጥሩነቷን በተደጋጋሚ በመለሰቻቸው ኳሶች ስታሳይ የታየችሁ የድሬዳዋዋ ግብ ጠባቂ ሂሩት ደሴ እንደ ምንም አድናባታለች፡፡
ከእረፍት መልስ ንግድ ባንኮች ያደረጉት የተጫዋች ለውጥ ውጤት ይዘው እንዲወጡ ያደረጋቸው ሆኗል፡፡ ሎዛ አበራ እና የቀኝ መስመር ተከላካይዋ ዓለምነሽ ገረመውን በማስገባት ብዙነሽ ሲሳይን እና ብርቱካን ገብረክርስቶስን ለውጠው አስወጥተዋል፡፡ ሎዛ አበራ ተቀይራ በመግባት ሜዳ ላይ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ብታደርግም የድሬዳዋ ተጫዋቾች አላፈናፍን በማለታቸው ያገኘቻቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻለችም ሆኖም ሎዛን ለመያዝ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ የቡድኑን የመከላከል ሚዛን ድሬዳዋዎች መጠበቅ አልቻሉም፡፡
በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ከመልበሻ ክፍል መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች ሁለት አጋጣሚን ቢያገኙም ፍፁም የአጨራረስ ክፍተት ግን በአጥቂዎቹ ላይ ይታይ ነበር፡፡ በተለይ ፀጋነሽ ወራና በግራ በኩል ወደ ግብ የሞከረቻት እና የግቡ ብረት ያዳነባት ምናልባትም የምስራቁን ክለብ መሪ ልታደርግ ትችል የነበረች ብትሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ሆኖም ደቂቃው እየገፋ በመጣ ቁጥር ወደ መከላከሉ ያዘነበሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በመከላከል የአቋቋም ስህተት ግብ አስተናግደዋል፡፡ አረጋሽ ካልሳ ግብ አስቆጥራ ከጨዋታ ውጪ ከተባለ ሦስት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ 78ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ገረመው በቀኝ በኩል የተገኘን ቅጣት ምት ወደ ግብ ስታሻማ ተጨራርፎ ሰናይት ቦጋለ ጋር ደርሶ ተጫዋቿም አንድ የድሬዳዋ ተከላካይ ቀንሳ ስታሻማ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ህይወት ደንጊሶ በግንባር በመግጨት ንግድ ባንክን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ በ81ኛው ደቂቃም ላይ እመቤት አዲሱ በሚገባ በቅንጅት የመጣ ኳስ እግር ላይ እንደደረሰ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርራ በመምታት ሁለተኛ ግብ ለንግድ ባንክ አክላለች፡፡
የዳኛዋ ፊሽካ ሊሰማ ደቂቃዎች ሲቀሩት ድሬዳዋዎች ጫና ለመፍጠር ታትረዋል፡፡ ሊና መሐመድ ብረት የመለሰባት አስቆጪ ዕድላቸው ብትሆንም በንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ለንግድ ባንክ ውጤታማነት ተጠቃሽ የነበረችው ህይወት ደንጊሶን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡
-በዛሬው ጨዋታ ከታዘብነው የዘንድሮው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ 19 ቫይረስ የተነሳ በዝግ ስታዲየም ይደረጋል የሚል ህግ ቢቀመጥም በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ላይ ግን በርካታ ደጋፊዎችን ተመልክተናል፡፡ በየጨወታው በርካታ የክለብ ተጫዋቾች ለኮቪድ 19 ተጋላጭ በመሆናቸው ክለቦች እየተቸገሩ ከመሆኑ አኳያ ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን መጠቆም እንወዳለን። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ፍራንኮ በሰጡን ምላሽ “የጤና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ውድድሮች በበርካታ ተመልካቾች እየተደረገ በመሆኑ በቀጣይ የሚስተካከል ካልሆነ የወንዱንም ሆነ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከሰው ህይወት ስለማይበልጥ እንሰርዘዋለን።” በማለት ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ መላኩን ነግረውናል፡፡ ይህም ከመሆኑ በፊት የሚመለከተው አካል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ