3ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህኛው ሳምንቱ የታዘብናቸውን ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፋችን ዳሰናቸዋል።
👉በመልካም ጅማሮው የቀጠለው ሀዲያ ሆሳዕና
የአሸናፊ በቀለው ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪምየር ሊግ እስካሁን ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሦስቱንም በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥቦች ሊጉን በአንደኛነት እየመራ ወደ አራተኛ የጨዋታ ሳምንት የሚያመራ ይሆናል።
በዚህኛው ሳምንት ያለ ወሳኙ ተጫዋቹ ዳዋ ሆቴሳ ሲዳማ ቡናን የገጠመው ቡድኑ በሦስቱ የውጭ ዜጋ ተጫዋቾቹ ግቦች ታግዞ 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
ምንም እንኳ ካለፉት ዓመታት በመነሳት የሊጋችን ቀጣይ ሁኔታን ለመገመት እጅግ አዳጋች ቢሆንም ቡድኑ አሸናፊ በቀለ የሚታወቁበት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀትን የተላበሰ እና ለዚህም ትግበራ የሚረዱ በርካታ ተጫዋቾችን የያዘ መሆኑ ቢያንስ ከጨዋታዎች ነጥብ ይዞ ለመውጣት እንደሚረዳው ይታመናል። የስብስቡ ጥራት፣ ጥልቀት እና ተግባቦትም የቡድኑን ቀጣይ ጉዞ መልክ ሊያሲዘው እንደሚችል የሚጠበቅ ሲሆን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች እንደታየው የአንጋፋ ተጫዋቾች ልምድ እና እና የተቀያሪ ተጫዋቾች ውጤት የመቀየር ሁኔታ ለቡድኑ ውጤት ማማር ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚህም ነብሮቹ በዚህ አጀማመራቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ከዓምናው ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ በሊጉ ተፎካካሪ ቡድን ሆነው የሚዘልቁ ይመስላሉ።
👉ሀዋሳ ከተማ ዓመቱን እንዴት ይዘልቀው ይሆን?
በ3ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አስደንጋጭ የሆነ የ4-1 ሽንፈት አስተናግደዋል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንትም በተመሳሳይ በሰበታ ከተማ ከጨዋታ ብልጫ ጋር የ3-1 ሽንፈትን ያስተናገደው ቡድኑ ከወዲሁ “የውድድር ዘመኑን እንዴት ይዘልቀው ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል።
እስካሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ከአብዛኛዎቹ ቡድኖች በአንድ ያነሰ ጨዋታን አድርጎ ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የሀዋሳ ከተማ የመከላከል አደረጃጀት በሊጉ እስካሁን የታየው ደካማ የተከላካይ መስመር ነው። ላለፉት አመታት በመከላከሉ ረገድ በነበረው ድክመት ይተች የነበረው ቡድኑ ዘንድሮም ይህን ችግሩን የቀረፈ አይመስልም። በጉዳት እና በሌሎች ምክንያቶች በመጀመሪያው ጨዋታ ከተጠቀመበት ስብስብ በዚህኛው ሳምንት የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርግ በተወሰነ መልኩ መሐል ሜዳ ላይ ኳስን ለመቆጣጠር ከመሞከር በዘለለ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ይህ ነው የሚባል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በሁለቱም ጨዋታዎች ማሳየት ተስኖታል።
ከሌሎች ክለቦች አንፃር ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ፍንትው አድርገው ያሳዩ ሁለት ጨዋታዎችን ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ከዋና አሰልጣኛቸው ሙሉጌታ ምህረት በዋና አሰልጣኝነት የማሰልጠን ልምድ አለመኖር ጋር ተዳምሮ የዘንድሮው የውድድር ዘመንን በምን መልኩ ይገፋዋል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ይመስላል።
ሀዋሳ ከተማ በቀጣዩ የ4ኛ ሳምንት መርሃግብር ደግሞ ሁለት ተከታታይ ድሎችን ካስመዘገበው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ፈታኝ የሆነ ጨዋታ ይጠብቀዋል።
👉ካለፉት ጨዋታዎች የተሻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር የተስተዋለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንገብጋቢ ለነበረው ችግራቸው አቤል ያለው መፍትሔን ይዞላቸው የቀረበ ይመስላል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኳስን መቆጣጠር ላይ ያመዘነ አቀራረብ ሲከተል የነበረው ቡድኑ የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት እና የግብ እድሎችን ለመፍጠር በእጅጉ ሲቸገር የተስተዋለ ሲሆን ዘንድሮም ይህ አቀራረቡ በፊት መስመር ካስፈሰማቸው ተጫዋቾቹ ባህርይ ጋር እንዴት ይጣጣም ይሆንሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል። ባለፊት ሁለት ጨዋታዎች እንደታየው ግን ቡድኑ ከዚህ ቀደም የሚታወቅበት ቀጥተኝነቱን ይዞ በመቅረብ ሰባት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ለዚህ ደግሞ የፈጣኑ አቤል ያለው ሚና ከፍተኛ ነበር።
አቤል ያለው በደመቀበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሀዋሳ ከተማን 4-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከፋሲሉ ሽንፈት መልስ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል። በጨዋታው ከጉዳት የተመለሰው ጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አዲሱ ፈራሚው ሮቤን ንጋላንዴና የሀዋሳ ከተማው ዳዊት ታደሰ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ግብ ፈረሰኞቹ ሀዋሳን መርታት ችለዋል።
በበርካታ አማራጮች የተሞላው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ዘንድሮ ካለፉት አመታት በተሻለ ቡድኑን ወደ ቀደመው ክብሩ የመመለስ ግዴታን ተሸክሞ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሰበታ ከተማን የሚገገጥም ይሆናል።
👉 “አንድ ወደ ፊት ሁለት ወደኋላ” ተጓዡ ወላይታ ድቻ
በሊጋችን የቡድኖች አቋም መዋዠቅ ጉዳይ ተደጋግሞ የሚነሳ ነጥብ ሆኖ እና አምነን ተቀብለነው የውድድሩ አንድ መገለጫ አርገን ከወሰድነው ሰነባብተናል።
ሆኖም አልፎ አልፎ አንዳንድ ቡድኖች በአንድ ጨዋታ ልዩነት በተናጠል የተጫዋቾች ብቃትም ሆነ በቡድን ሥራ አጀብ አሰኝተውን ሲያበቁ በቀጣዩ ግጥሚያ ‘ዓይኔ ነው ?’ የሚያስብል የወረደ ብቃት ሲያሳዩን እንደአዲስ ለመገረም እንገደዳለን።
በዚህ ሳምንት በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት የደረሰበት ወላይታ ድቻ ጉዳይም ከዚህ የተለየ አልነበረም። ሁለተኛው ሳምንት ላይ አዳማን የረታው ድቻ እንደ እንድሪስ ሰዒድ ፣ ስንታየሁ መንግሥቱ፣ በረከት ወልዴ ዓይነት ተጫዋቾችን በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ማካተት ተችሎ ነበር። እንደ ቡድንም በጨዋታው ክፍለ ጊዜ ወጥ የሆነ፣ የቡድንን አቅም ቆጥቦ ያለድካም የተጫወተ፣ ጨዋታውን በሚፈልገው መንገድ ያስኬደ ድንቅ ቡድን ሆኖ ነበር።
ብዙ ለውጥ ሳያደርግ ወልቂጤን የገጠመው የሦስተኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ ደግሞ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ አቋም ቆሌው ርቆት ተስተውሏል። ከመክፈቻው ሽንፈት በኋላ በድንቅ ብቃት ወደ ድል የመጣው ቡድንም ዳግም ወደ ሽንፈት ተመልሷል። በእርግጥ ከሜዳ ውጪ የቡድንን አቋም የሚቀያይሩ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ቡድኖቻችን በዚህ መጠን ሲለዋወጡ ማየት ጥንካሬያቸውን ጭምር እንድንጠራጠር የሚያደርገን ነው።
👉ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ቡና
በ3ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እጅግ አወዛጋቢ የነበሩ የዳኝነት ውሳኔዎች በተስተዋሉበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 3-2 ማሸነፍ ችሏል።
ያለ አቡበከር ናስር ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህኛው ጨዋታም ገና ከጅምሩ ነበር ሌላኛውን ተጫዋቻቸው ሚኪያስ መኮንን’ን በጉዳት ያጡት። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሀብታሙ ታደሰ ደርሶላቸው ሁለት ግቦችን በጨዋታ እንዲሁም አማኑኤል ዮሐንስ ደግም ተጨማሪዋን በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ግቦች ከጨዋታው መሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችለዋል። እስካሁን ድረስ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደው የካሣዬ አራጌ ስብስብ ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን በማሳካት መልካም የሚባል የውድድር ዘመን ጅማሮ እያደረገ ይገኛሉ።
ባለፉት ዓመታት ደካማ አጀማመር በማድረግ እና ቀስ በቀስ ወደ ውድድሩ ቅኝት በመግባት ጥለውት የነጎዱ ቡድኖችን ጭራ ለመያዝ ሲጣጣር የሚስተዋለው ቡድኑ ውጤቱን ለማስተካከል በከፍተኛ ጫና ሲጫወት መመልከት አዲስ አይደለም። ዘንድሮ ከወዲሁ ነጥቦች መሰብሰብ መጀመሩ ሳምንታት በገፉ ቁጥር የሚኖረውን የተጠባቂነት ጫና ይቀንሰዋል ባይባልም የቡድኑን በራስ መተማመን እና የአሸናፊነት ስነ-ልቡና ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ከጨዋታ የበላይነት ጋር ወደ አሸናፊነት የተመለሱት ፋሲል እና ባህር ዳር
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በቁጥር ብልጫ ኖሯቸው በኢትዮጵያ ቡና 3-1 መሸነፋቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞን ያስተናገዱት ፋሲል ከነማዎች እንዲሁም በሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ሽንፈትን ያስተናገዱት ባህርዳር ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደካማዎቹን ጅማ አባ ጅፋርና አዳማ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።
የፋሲል ከነማ ፍፁም የበላይነት በታየበት የሐሙሱ ጨዋታ ዐጼዎቹ ድንቅ በነበረው ሽመክት ጉግሳ እንቅስቃሴ ታግዘው አራት ግቦችን አስቆጥረው ማሸነፍ ችለዋል። ለፋሲል ግቦቹን ሽመክት ጉግሳ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሙጂብ ቃሲምና ሳሙኤል ዮሐንስ ማስቆጠር ችለዋል።
በአንፃሩ ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ አዳማ ከተማን 2-0 በሆነ ውጤት በመርታት ከሽንፈታቸው አገግመዋል። ባዬ ገዛኸኝና ልማደኛው ፍፁም ዓለሙ የግቦቹ ባለቤት ናቸው።
👉 የወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ድል
3ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የጨረሱት ወልቂጤ ከተማዎች ሀሙስ ዕለት ወላይታ ድቻን 2-1 በሆነ ውጤት በመርታት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች እድሎችን እየፈጠሩ መጨረስ ባለመቻላቸው ብቻ ነጥብ ለመጋራት ተገደው የነበሩት ሠራተኞቹ በወላይታ ድቻው ጨዋታ ከቀደሙት ጨዋታዎች አንፃር ያነሰ ነገርግን ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እድሎችን ፈጥረው በተስፈኛው ያሬድ ታደሰ ልዩነት ፈጣሪነት ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብን ይዘው መውጣት ችለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ