በሦስተኛ ሳምንት የታዩ ዐበይት ጉዳዮችን የምናጠናቅቀው በዚህ የአራተኛ ክፍል መሰናዶ ነው።
👉ምስረታቸውን እየዘከሩ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህር ዳር ከተማ
በኢትዮጵያ እግርኳስ ከቀዳሚዎቹ ክለቦች ተርታ የሚመደበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በውል ቀኑ ባይታወቅም በ1928 ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ ስለመመስረቱ ታሪክ ያወሳል። በኢትዮጵያ የእግርኳስ ክለቦች ውድድር በድልና ስኬት የደመቁ 85 ዓመታትንም ማሳለፍ ችሏል።
ታሪኩንና ክብሩን ጠብቆ በሀገራችን እግርኳስ ላይ ከፊት ሆኖ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው የምንጊዜም ጊዮርጊስ ካፒታልስ ዓይነት ልኩን በሚመጥን የፕሮፌሽናል አደረጃጀትና የስፖርት መሠረተ ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ራሱን የማዘመን የቤት ሥራን ሰንቆ 85ኛ የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል።
በተመሳሳይ በ1973 ምስረታውን ያደረገውና 40 ዓመቱን የደፈነው የጣናው ሞገድ ባህር ዳር ከተማ ሌላኛው በዚህኛው ሳምንት ምስረታውን እየዘከረ የሚገኝ ክለብ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የውድድር መድረኮች የመሳትፍም ሆነ የውጤት ታሪክ የሌለው ክለቡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እጅግ ከፍተኛ እምርታን እያሳየ ይገኛል። 40ኛ ዓመቱ ላይ የደረሰው ክለቡ በቀጣይ የተጀመሩትን አመርቂ ሥራዎች በማስቀጠል ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመድረስ እየተጋም ይገኛል።
👉አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎችን ያስተናገደው የቡና እና ድሬዳዋ ጨዋታ
በ3ኛ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 3-2 የረታበት ጨዋታ እጅግ አደናጋሪ የነበሩ የዳኝነት ውሳኔ የተስተዋሉበት ጨዋታ ነበር።
ዋና ዳኛ ብርሃኑ መኩርያ በመሐል ዳኝነት በመሩት ጨዋታ በርካታ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ እና ጨዋታውን በአግባቡ የመቆጣጠር ድክመት ተስተውሏል። ለአብነት ያክልም ለድሬዳዋ ከተማ የአቻነቷን ግብ በ27ኛው ደቂቃ ኢታሙና ኬይሙኒ ካስቆጠረ በኃላ በቀኝ ከማን አንሼ ባለ ወንበሩ አካባቢ ተቀምጠው ወደነበሩት የክለቡ ደጋፊዎች አቅንቶ ከደጋፊዎች ጋር በንክኪ ደስታውን የገለፀበት መንገድ ከኮቪድ ፕሮቶኮል አንፃር በዝምታ መታለፉ፣ በ35ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ፍፁም ቅጣት ምቱን ከመምታቱ በፊት በርካታ ተጫዋቾች ወደ ሳጥኑ መግባታቸው፣ በ55ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን ለሀብታሙ ታደሰ ለማቀበል የለከውን ኳስ ለማቋረጥ በረከት ሳሙኤል በገባው ሸርተቴ ኳስ በእጁ ባልተነካበት ሁኔታ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት (ምንም እንኳ በቪድዮ ምልሰት ካልታየ በቀር ለቅፅበታዊ ዕይታ እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም) በግልፅ የታዩ የተሳሳቹ የዳኝነት ውሳኔዎች ሲሆኑ የዳኛው ዕይታ እና ውሳኔ ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማዎች ያገኙት የፍፁም ቅጣት ምት፣ በቢጫ ብቻ የታለፉት ዳንኤል ደምሴ እና አበበ ጥላሁን የሰሯቸው ከባድ ጥፋቶች እንዲሁ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ የታየባቸው ነበሩ።
👉የደጋፊዎች አዲስ የጨዋታ ዕለት ልማድና በስታዲየም የሚታደሙ ደጋፊዎች ጉዳይ
ከኮቪድ 19 መከሰት ወዲህ በርካታ ሰዎችን በአንድ ላይ ያገናኙ የነበሩ ሁነቶች አሁን ላይ በጥቂት ሰዎች በላቀ ጥንቃቄ እንዲደረጉ ገደብ መጣሉን ተከትሎ እንደ ሌሎች መስኮች ሁሉ በስፖርቱ ዘርፍ ስታዲየሞች ፀጥ ረጭ ካሉ ሰነባብተዋል።
አዲሱ የውድድር ዘመን ከቀናት በፊት ሲጀመር ሊጉን በበላይነት የሚመራው አክሲዮን ማኅበር ቁጥራቸው የተመጠኑ ደጋፊዎች ስታዲየም ተገኝተው ቡድናቸውን እንዲያበረታቱ ፈቃድ ቢሰጥም አፈፃፀም ላይ መጠነኛ ክፍተቶች መኖራቸው ቅሬታ ሲያስነሳ ነበር። በዚህኛው ሳምንት ግን ከጨዋታዎች መጀመር በፊት በፀጥታ አካላት በስታዲየም የታደሙ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መጠን ከተፈቀደው በተናጥል አስር አስር ደጋፊዎች ጋር ስለመስማማቱ ቆጠራ ሲደረግ አልፎም ከቁጥር እላፊ የመጡ ደጋፊዎች ከስታዲየም እንዲወጡ ሲደረግ ተስተውሏል። ይህም ይነሳ ለነበረው የፍትሃዊነት ጥያቄ አፈጣኝ ምላሽ የሰጠ መልካም ጅምር ነው።
እልፍ ለሆኑት የየክለቦቹ ደጋፊዎች የዘንድሮው ውድድር በሱፐር ስፖርት የቀጥታ ሽፋን በማግኘቱ የሚወዱትን ክለባቸውን በዓይናቸው ለማየት ባይታደሉም በቴሌቪዥን መስኮት ግን ጨዋታዎችን የመታደም እድሉ ተመቻችቷል። ታድያ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎች በጨዋታ ዕለት በተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው የክለባቸውን ጨዋታ የመመለከት ብሎም በመዝናኛ ስፍራ ትንሿን ካምቦሎጆ የመፍጠር አዲስ የጨዋታ ዕለት ልማድ በስፋት እየተቀጣጠለ ይገኛል።
👉ማራኪዎቹ የፋሲል ከነማና የድሬዳዋ ከተማ መለያዎች
ከክለቡ የመለያ ቀለም ውጭ የሆነ አዲስ የቀለማት ህብር መለያን በመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ያስመለከተን ድሬዳዋ ከተማ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የክለቡን ይፋዊ መገለጫ ቀለማት ውስጥ አንዱ በሆነው በብርቱካናማ ቀለም ደረቱ ላይ ቢጫ የፀሀይ ወጋገን ያረፈበት አዲሱ መለያቸው እጅግ ማራኪ ነው። ከቀለመት ስብጥሩ ባለፈ ከመለያው በስተጀርባ የሰፈረው የተጫዋቾች መለያ ቁጥር እና ስም በጉልህ በሚታይ መልኩ የሰፈረበት ይህ መለያ በጥቅሉ እጅግ የተዋበ ነው።
በተመሳሳይ ፋሲል ከነማዎች ባሳለፍነው የውድድር አመት በአዲስአበባ መቀመጫውን ካደረገ አንድ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከተሰማራ ባለሀብት በስጦታ መልክ የተበረከተላቸውን ለእይታ ማራኪ የነበረውን ነጭ መለያ ከጥቁር ቁምጣ ጋር የሆነውን መለያ ከረጅም ጊዜ በኃላ በዚህኛው ሳምንት በጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ ለብሰውት ወደ ሜዳ ገብተዋል።
👉ለአሰልጣኞች ዕይታ ፈታኝ የሆነው የካሜራ ማቆሚያ
በአዲስ አበባ ስታዲየም የጨዋታውን የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን የሚሰጠው ሱፐር ስፖርት ጨዋታውን ከተለያየ አቅጣጫ ለመቅረፅ ይረዳው ዘንድ ካሜራ የሚቀመጥባቸውን ማማዎችን በተለያየ የሜዳ ክፍሎች አስቀምጧል።
ከእነዚህም አንዱ የሆነውና በንፅፅር በቁመቱ ከሌሎቹ ያነሰውና ለሜዳው በቀረበ ሁኔታ በሜዳው አጋማሽ የተተከለው ማማ ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ከሚቀመጡበት ቦታ ሆነው አጠቃላይ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ለማቃኘት እክል ሲፈጥር ተስተውሏል። ይህን ሁኔታ ለመቅረፍ የአሰልጣኞች የመቀመጫ ቦታ በጊዜያዊነት በመቀየርም ሆነ የማማውን ቦታ በመቀየር መቀረፍ ይኖርበታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ