ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

ከ3ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጠናቀቅ በኋላ የተመለከትናቸው ዓበይት አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፍ ተዳሰዋል።


👉የአሰልጣኝ አብርሃም እና ውበቱ በጋራ መታየት

ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሀዋሳ ከተማ ባገናኘው የ3ኛ ሳምንት መርሐግብር እና ቀጥለው በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና የአሁኑ የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ በጋራ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተቀምጠው ጨዋታውን መመልከታቸው ትኩረትን የሳበ ነበር።

ከብሔራዊ ቡድን ቅጥር ጋር በተያያዘ በርካታ የሴራ ንድፈ ሀሳቦች እና ጉዳዮች ሲነሱ እንደመቆየታቸው በሁለቱ አሰልጣኞች መካከል ችግር ያለ እስኪመስል ድረስ በመገናኛ ብዙሀን ከፍተኛ የጡዘት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ሆኖም ሁለቱ በአንድ ላይ ተቀምጠው መታየታቸው ቢያንስ በአሰልጣኞቹ መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዳለ ማሳያ ሆኖ ታይቷል።

በጋራ ለመሥራት ሩቅ ስለመሆናቸው የሚታሙት የሀገራችን አሰልጣኞች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በተወሰኑ አሰልጣኞች በኩል ሀሳቦችን በቀናነት የመለዋወጥና የመማማር ፍላጎቶች ብሎም ተግባራዊ ጥረቶች ሲያደርጉ ይስተዋላል። የውበቱና አብርሃም በጋራ በስታዲየም ታድመው ጨዋታ የመመልከታቸው ጉዳይም የዚህ መገለጫ ነው።

በመጠላለፍ እና በጥሎ ማለፍ አስተሳሰብ በታጠረው እግርኳሳችን መሰል የቀና አስተሳሰብ ጅምሮች ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው።

👉መረጋጋት የማይታይባቸው አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመ ልሳን

በአጠቃላይ እግርኳሳችን ከሚታዩ ሁነቶች አንዱ የአሰልጣኞች በጨዋታ ላይ የሚታይ እረፍት አልባነት እና ቁንጥንጥነት ነው። በእርግጥ ይህ ዘንድሮ በእጅጉ ቀንሶ የታየ ሲሆን የዚህ ምክንያቱ ይህ ባህርያቸው “በሱፐር ስፖርት እንዳይታይ ይሆን?” የሚያስብል ነው።

በዚህ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ የድሬዳዋው አሰልጣኝ ቡድኑን ይመራበት የነበረው መንገድ፣ ከረዳቶቹ ጋር የነበረው ግንኙነት እና የዳኞቹ ጋር የሚያሳየው እሰጥ እገባ ቡድኑ እንዳይረጋጋ የሚያድርግ ነበር። በእግርጥ የነበረው የዳኝነት ሁኔታ የጨዋታውን መልክ የቀየረ ቢሆንም አሰልጣኙ ቡድኑን በማረጋጋት ከጨዋታው ይዘው መውጣት የሚገባቸውን ውጤጥ ይዘው ለመውጣት መትጋት ሲገባቸው ይብሱኑ አሰልጣኙም ሆነ ተጫዋቾቹ ስሜት ውስጥ ገብተው ለሁለት ቀይ ካርድ እና አሰልጣኙ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆነዋል። ምናልባትም ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ በጨዋታው እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ቢሆን ኖሮ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጎል እንደማስቆጠራቸው ተጨማሪ ጫና ፈጥረው አንድ ነጥብ ይዘው ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ ሊፈጠር ይችል ነበር።

አሰልጣኙ ባለፈውም ሆነ በዚህ ሳምንት ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት በዳኛ ያልተገቡ ውሳኔዎች ላይ ምሬታቸውን የገለፁ ሲሆን ቅሬታቸውን መግለፃቸው አግባብ ቢሆንም የሚገልፁበት መንገድ ቡድኑ ላይ በቀጣይ “ምንም ብናደርግ በዳኛ እንሸነፋለን” የሚል የተበዳይነት ስነልቦና እንዳይሰርፅበት እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ውጤት ይዞ መውጣት ላይ ትኩረት እንዳያድርጉ ሊያደርጋቸው ይችላል።

👉ደግአረገ ይግዛው…

በሊጉ ከተሰረዘው የውድድር ዓመት ውጪ ልምድ የሌላቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው መልካም የጨዋታ አቀራረብ እና ተጫዋቾችን የማጎልበት ችሎታቸው እየታየ ይገኛል። የማጥቃት እና ኳስ የመቆጣጠር አቀራረብን የሚመርጡት አሰልጣኙ በዚህ ሳምንት ቡድናቸው ወላይታ ድቻን በረታበት ጨዋታ ላይ የነበረውን የመጀመርያ ተሰላፊዎች ዝርዝር ስንመለከት ከአብዱራህማን ሙባረክ ውጪ የአጥቂ ተጫዋች ያልነበረ ሲሆን በርካታ የአጥቂ አማካዮችን በመጠቀም ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ ተቆጣጥረው ወጥተዋል። በክህሎት የደረጀውን የወላይታ ድቻ የአማካይ ክፍልን በጉሎበተኛ እና የመከላከል ባህርይ ባላቸው አማካዮች ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ በመሐለኛው የሜዳ ክፍል በቁጥር በልጠው የሚፈልጉትን አሳክተዋል።

አሰልጣኙ የተጫዋቾችን ብቃት በማጎልበት ረገድም ጥሩ አቅም እንዳላቸው ፍንጭ እየሰጡ ይገኛሉ። ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ባሳየው ድንቀረ አቋም መነሻነት ብዙ ተጠብቆበት የመሰለፍ እድል በማጣት እንደታሰበው መጎልበት ያልቻለው ጫላ ተሺታ ዓምና በወልቂጤ በድጋሚ አብቦ የታየ ሲሆን ዘንድሮም በተመሳሳይ ለተከታታይ ዓመታት በድሬዳዋ እምብዛም ዕድል ያላገኘው ያሬድን እንዲደምቅ እድል መስጠታቸውና ተጫዋቹም ከወዲሁ መፍካት መጀመሩ ለሌሎች አሰልጣኞች ትምህርት የሚሆን ነው።

ዐበይት አስተያየቶች

👉ፍሰሀ ጥዑመልሳን በዳኝነቱ ላይ ያቀረበው የሰላ ትችት…

“ዳኝነቱ ልክ አይደለም በአጠቃላይ ፤ በጣም ነው የሚያሳዝነው። በ ዲ ኤስ ቲቪ እየታየ እንኳን በሥነ ስርዓት አይዳኙም እንዴ ? በጣም ነው የማዝነው። ፍፁም ቅጣት ምት እኛን ይከለክላሉ ለእነሱ ግን ይሰጣሉ። እንዴት ነው ታድያ ማሸነፍ የሚቻለው ? ብቻ በጣም ያሳዝናል።”

👉ፋሲል ተካልኝ በሁለተኛው አጋማሽ ስለተዳከመው የቡድኑ እንቅስቃሴ…

“በሁለት ዓይነት መንገድ ነው። የመጀመሪያው ትንሽ ፍጥነታችንን ቀንሰን የተጋጣሚያችንን ክፍተት ለመፈለግ በማሰብ ነው። በዛው ልክ ሁለት ጎል ከማግባታችን አንፃር በጣም ተጨንቀን ቶሎ ቶሎ የግብ ዕድል ለመፈለግ ዕድሉ የለንም። ምክንያቱም ከሁለት ከሦስት ቀን በኋላ ወሳኝ የሆኑ ጨዋታዎች ስላሉንን ተጫዋቾቻችንን መጠበቅ አለብን። በዛው ልክ ደግሞ የባለፈውም የዛሬውም ጨዋታ ግጭት የበዛበት ነበር። ተጫዋቾች ከሚገባው በላይ ጉልበት እየተጠቀሙ ነው። የመሸነፍ እና የማሸነፍ ጉዳይ አይደለም። እዚህ ውስጥ ተጫዋቾቻንን እንዳናጣ በጣም እፈራለሁ እና ዳኝነቱም ትኩረት ቢደረግበት ለማለት እፈልጋለሁ።”

👉ሥዩም ከበደ ስለ ሽመክት ጉግሳ…

“ሽመክት ጥሩ ነበር። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ተሳትፎ ድንቅ ነበር። በጨዋታው የነበረውም ፍላጎት ትልቅ ነበር። እርግጥ እርሱ ጨዋታ ላይ ብቻ ሳይሆን ልምምድ ላይም እንደዚሁ ነው። ከዚህም በላይ መሻሻል ስለሚችል ግን አሁንም መጠንከር አለበት።”

👉ጳውሎስ ጌታቸው ስለ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞ…

“የሚያግዘኝ አካል ካለ ብሩህ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ። ዓምናም እንደምታቁት በውጥንቅጦች ውስጥ ነበር የሰራሁት። እንደዛም ሆኖ ውጤታችን መጥፎ አልነበረም። ትላልቅ ቡድኖችን ነጥብ እናስጥል ነበር። ዘንድሮ ግን እንደ ዓምናው ሰፊ የዝግጅት ጊዜም አልነበረንም። እኔ ግን መናገር የምፈልገው አቅሜ እስከፈቀደው ድረስ የምችለውን እንደምሰራ ነው።”

👉ሙሉጌታ ምህረት ስለ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት

“ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዴት እንቆጣጠር የሚለውን ተነጋግረን ነበር። በተለይ ደግሞ የመስመር ላይ እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር አስበን ነበር። ግን ያንን ማድረግ ሳንችል ጊዮርጊሶች በመስመር ላይ አጥቅተውን ግቦችን አስቆጥረውብናል። ከጨዋታ ጨዋታ ከኳስ ጋር ያለን ነገር እየተሻሻለ ነው ብዬ አምናለው። ይህ ቢሆንም ግን እንደ ቡድን አልተደራጀንም። ለቀጣዩ ጨዋታ ግን ጠንክረን እንቀርባለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ