ላለፉት ቀናት ሲካሄድ ከቆየው የ3ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ ትኩረትን የሳቡ ዓበይት ተጫዋች ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፍ ተዳሰዋል።
👉ሁሉም ላይ ያለው – አቤል ያለው
በሐረር ሲቲ እና ደደቢት የምናውቀው አቤል ያለው ከዓመት ዓመት ለውጥ እያሳየ እና እያደገ ቁልፍ ተጫዋች መሆን የቻለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ፈጣኑ አጥቂ በተለይ ከመስመር በመነሳት ኳስ እየገፋ ወደ ውስጥ ሲገባ ለተጋጣሚ ተከላካዮች ለማቆም አስቸጋሪ ሆኖ ይታያል። በእርግጥ አቤል ግቦችን ማስቆጠሩ አዲስ ነገር ባይሆንም በዚህ ሳምንት ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከተማን በረታበት ጨዋታ ደግሞ ኳስ እና መረብን አያገናኝ እንጂ የግቦቹ ሁሉ መነሻ ሆኖ ምርጥ ብቃቱን አሳይቶናል።
ቡድኑ ቀዳሚ የሆነበትን ጎል ለሮቢን ንግላንዴ ሲያቀብል ቀጣዩ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል እሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ነበር የተቆጠረው። ቀጥሎም ሦስተኛውን ግብ ለጌታነህ ከበደ አመቻችቶ ሲያቀብል ሀዋሳዎች ራሳቸው ላይ ያስቆጠሩት አራተኛ ግብም እርሱ ካነሳው የማዕዘን ምት የተገኘ ነበር። ይህ የጨዋታ ውሎም ከአማካይ ሳይሆን ከአጥቂ መስመር ተጫዋች መሆኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል።
ተጫዋቹ ፈጣን እና ድንቅ የቴክኒክ ክህሎት እና እይታ ያለው ከመሆኑ አንፃር አሰልጣኝ ዴቪድ ማሒር ቡድናቸውን በሱ ዙርያ እንደሚሰሩ ያለፉት ጨዋታዎች እንቅስቃሴ ፍንጭ የሚሰጥ ሲሆን ለተጫዋቹ ክፍተት የሚሰጥ ፈጣን ሽግግር የተላበሰ የማጥቃት አጨዋወት አቤልን ይበልጥ እንደሚያጎላው ይታመናል።
👉ያልተዘመረለት ሽመክት ጉግሳ
በወላይታ ድቻ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ደደቢት በመስመር አጥቂነት እና አማካይነት ሚና የምናውቀው ሽመክት በፋሲል ከነማም በወሳኝ ተጫዋችነቱ ቀጥሏል። የሚጫወትበትን ቡድን የመስመር የማጥቃት እንቅሳቃሴ አስፈሪ በማድረግ እንዲሁም ወደ ኋላ እየተመለሰ ጓደኞቹን በመከላከሉ በማገዝ በታታሪነት ሲለፋ ይስተዋላል። ይህ የሜዳ ላይ ባህሪውም በቶሎ ዓይን ውስጥ እንዲገባ እና ወሳኝ ተጫዋች ሆኖ እንዲነሳም ያደርገዋል።
ሽመክት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ፋሲል ጅማ አባ ጅፋርን ሲገጥም ያሳየው አቋም ደግሞ እውነትም ትከረት ሳቢ ነበር። የቡድኑ የመጀመሪያ የቅጣት ምት ግብ ሲቆጠር የተጠለፈው ሽመክት፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛው ጎል በሙጂብ ቃሲም እና ሳሙኤል ዮሐንስ ሲቆጠር አቀባይ ሽመክት፣ አራተኛው ጎል ከመረብ ሲገናኝ ደግሞ አስቆጣሪው ራሱ ሽመክት በመሆን ደምቆ የታየበትን ጨዋታ አሳልፏል።
👉”ዳግማዊ ጫላ…” – ያሬድ ታደሰ
ዓምና በተሰረዘው የውድድር ዘመን ክስተት ከነበሩ ቡድኖች አንዱ በነበረው ወልቂጤ ከተማ ቡድን ውስጥ የጫላ ተሺታ ሚና እጅጉን የጎላ ነበር። በሲዳማ ቡና በቂ የመሰለፍ እድልን ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ወልቂጤ ከተማ ያመራው ጫላ በመከላከሉ ረገድ ጥብቅ በነበረው ስብስብ ውስጥ ወሳኝ የነበሩ አምስት ግቦችን በማስቆጠር እና የማጥቃት ሒደቱን በፊት አውራሪነት በመምራት የቡድኑ አለኝታ ሆኖ ነበር።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ጫላ ተሺታን በሲዳማ ቡና የተነጠቁት ወልቂጤ ከተማዎች ዓምና የቡድናቸው ቁልፍ ተጫዋች የነበረውን ተጫዋች ለመተካት አሜ መሐመድ እና አቡበከር ሳኒን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ማስፈረም ቢችሉም ተስፈኛው ያሬድ ታደሰ ግን ቡድኑን በፍጥነት በመላመድ በሠራተኞቹ ቤት ልዩነት ፈጣሪ እየሆነ መጥቷል።
በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ተቀይሮ የገባው ያሬድ ሜዳ ውስጥ በቆየባቸው ውስን ደቂቃዎች ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና አቻ ለመለያየት መነሻ የሆነችውን የቡድኑን መንፈስ የቀየረች ግብ ሲያስቆጥር ለመጀመሪያ ጊዜ በቋሚነት በጀመረበት የወላይታ ድቻው ጨዋታ ቡድኑን ለድል ያበቁትን ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
እስካሁን ካስቆጠራቸው ግቦች በላይ ግቦቹ የተቆጠሩበት መንገድ የተጫዋቹን ግላዊ የብቃት ደረጃ በግልፅ የሚያሳዩ ሲሆን ጫላ ተሺታ ከሚታወቅበት አስደናቂ ፍጥነት በተቃራኒው ከመስፈንጠር ይልቅ ቴክኒካል ተጫዋች የሆነው ያሬድ በወልቂጤ ቤት የጫላን ፈለግ ተከትሎ ራሱን ፈልጎ እያገኘ ይመስላል።
👉 ለሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች “አሁን ወይንም መቼም”
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአንፃራዊነት የተረጋጋ የቡድን ስብስብ ካላቸው ቡድኖች መካከል ሀዋሳ ከተማ ይጠቀሳል። ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ በርከት ያሉ ከራሱ የዕድሜ እርከን ቡድኖች የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾችን በዋናው ቡድን ዕድል መስጠቱ ከአብዛኛዎቹ የሊጉ ክለቦች በልዩነት በበጎ የሚጠቀስለት ነው።
ለወትሮም ቢሆን ለታዳጊ ተጫዋቾች ዕድል በመስጠት የማይታሙት ሀዋሳ ከተማዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ውበቱ አባተ በዋና ቡድን አሰልጣኝነት እንዲሁም በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ይመሩ የነበሩት ከውጤታማዎቹ የዕድሜ እርከን ቡድኖች ያለ ማቋረጥ አሁን ድረስ ተስፈኛ ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ እያሳደጉ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።
ቡድኑ በብዛት ተጫዋቾችን እንደማሳደጉ ግን በተለያዩ ወቅቶች ወደ ዋናው ቡድን ያሳደጋቸውን ተጫዋቾች ብቃት በማሳደግ ረገድ ያልተሰራ የቤት ሥራ ስለመኖሩ የቡድኑ ያለፉት ዓመታት ውጤቶች ምስክር ናቸው። ተጫዋቾችን በብዛት ማሳደጉ ዋነኛ ግቡን ሊመታ የሚችለው ያደጉት ተጫዋቾች ከዓመት ዓመት ራሳቸውን እያሻሻሉ ቡድንን መጥቀም ሲችሉ እንጂ በጅምላ ማሳደጉ በእግርኳሳዊ መመዘኛዎች በተጫዋቾች ግላዊ ሆነ ቡድናዊ ዕድገት ካልታጀበ ለዝውውር የሚወጣን ብር ለጊዜያዊነት ከማስቀረት በዘለለ ለቡድኑ በዘለቂታዊነት የሚኖረው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም።
ለማሳያነትም ባሳለፍነው ረቡዕ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 የተረታውን የሀዋሳ ከተማን ስብስብ ብቻ ነጥለን ብንመለከት
ዳንኤል ደርቤ – በቡድኑ እና ሌሎች ክለቦች ከ10 ዓመት በላይ የተጫወተ
አዲስዓለም ተስፋዬ – በቡድኑ ከ10 አመት በላይ የተጫወተ
ደስታ ዮሐንስ – ወደ ዋናው ቡድን ካደገ 5 ዓመት የሆነው
ሄኖክ ድልቢ – ወደ ዋናው ቡድን ካደገ 5 አመት የሆነው
ዮሐንስ ሰጌቦ – ወደ ዋናው ቡድን ካደገ 5 አመት የሆነው
ቸርነት አውሽ – በዋናው ቡድን ደረጃ ከ2009 ጀምሮ በመጫወት ላይ ያለ
ተቀይረው የገቡ
ምንተስኖት እንድሪያስ – በዋናው ቡድን ደረጃ ከ2011 ጀምሮ በመጫወት ላይ ያለ
ዳዊት ታደሰ – በዋናው ቡድን ደረጃ ከ2009 ጀምሮ በመጫወት ላይ ያለ
ከላይ ለማሳያነት የቀረቡት ተጫዋቾች በተለያዩ ዓመታት ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ተጫዋቾች ናቸው።
ክለቡ እየተከተለ የሚገኘው ወጣት ተጫዋቾችን የማሳደግ አካሄድ ጤናማነቱ ባያጠያይቅም ይህ አካሄድ ግን ቡድኑ ላለፉት ዓመታት ለገባበት የውጤት ቀውስ እንደ ማምለጫ ሰበብ ሲቀርብ ይስተዋላል። እርግጥ ነው ቡድኖች ተፎካካሪ ሆነው እንዲዘልቁ የቡድኑን ጥራት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ተጫዋቾችን ማዘዋወር አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም ሀዋሳ ከተማ ከሚያሳድጋቸው በተጓዳኝ ከሌሎች ቡድኖች የሚያስፈርማቸው ልምድ እና በንፅፅር የተሻለ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች እንደመሆናቸው መጠን ያለፉት ጥቂት ዓመታት ውጤቶቹ ግን አመርቂ አልነበሩም።
ተጫዋቾች ከማሳደግ በትይዩ የሚቀርበው የተጫዋቾች የልምድ አልባነት ለአሰልጣኞችም ሆነ ለቡድኑ አመራሮች እንደ ምክንያትነት እያገለገሉ ቆይተዋል። ከዚህ እውነታ ባሻገር ቁልፉ እውነታ በክለቡ ከታችኞቹ ቡድኖች አድገው ብዙ እየተጠበቀባቸው አብዛኛዎቹ በሚያስብል ደረጃ ከማበብ ይልቅ እየከሰሙ ብሎም አንዳንዶቹ የቀደመ ማንነታቸውን በሚያጠራጥር ደረጃ ተዳክመው ይስተዋላል።
ዘንድሮ ግን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ በፈጠሩት አዎንታዊ ተፅዕኖ ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚጠሩ ተጫዋቾች አንዱ በሆነውና ከሀዋሳ ከተማ ለወጡ እግርኳሰኞች በሙሉ እንደ አርዓያ በሚታየው ሙሉጌታ ምህረት ስር መሰልጠናቸው ለተጫዋቾቹ ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ይተመናል። የሀዋሳ ከተማን ቤት ጠንቅቆ የሚያውቀው ሙሉጌታ ከጥቂት ዓመታት በፊት ባሳዩት ብልጭታ የት ይደርሳሉ ተብለው ተጠብቀው አሁን ላይ ግን ባሉበት የብቃት ደረጃ መልሰው እየረገጡ የሚገኙትን ተጫዋቾች በማነቃቃት አንዳች ለውጥ ይጠበቃል።
ተጫዋቾቹም ይህን አጋጣሚ እንደመጨረሻ ዕድል በመቁጠር ራሳቸው ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን ቡድኑ የትውልድ ሽግግር የማድረግ ግዴታ ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስልም።
👉ከጉዳት የሚመለሱ ተጫዋቾች አጠቃቀም
በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙም ትኩረት ከማይሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው የተጫዋቾች ከጨዋታና ከጉዳት መልስ የማገገም ሒደት እንደሆነ ይስተዋላል።
ለአሁኑ ለማንሳት የወደድነው ክለቦቻችን ከጉዳት የሚመለሱ ተጫዋቾች የሚይዙበትን መንገድ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይ ዓምና በቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳት ላይ የነበሩትን አስቻለው ታመነ እና ሰልሀዲን ሰዒድ፣ ጌታነህ ከበደ በተለያዩ ወቅቶች ወደ ሜዳ ለመመለስ በነበረው ጥድፊያ መነሻነት ተጫዋቾቹን ብሎም ቡድኑን ምን ያህል ለኪሳራ እንደተዳረጉ ይስተዋላል።
ድሬዳዋ ከተማዎች ብዙ ተስፋ አድርገውበት ከወልዋሎ ዳግም ወደ ክለባቸው የመለሱት ናሚቢያዊው ኤይታሙና ኬይሙኒ ከጉዳት መልስ ያለፉትን ቀናት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ስለሰራ ብቻ ተጣድፈው በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ቢያሰልፉትም ተጫዋቹ በሁለተኛው አጋማሽ ጉዳቱ በማገርሸቱ ተቀይሮ ለመውጣት በቅቷል።
ይህ የሚያሳየው ክለቦቻችን እንደ ኤይታሙና ኬይሙኒ ሁሉ መሰል የጉዳት ታሪክ ያላቸው ተጫዋቾችን በዘላቂነት በተሻለ መንገድ ለመጠቀም በቂ እረፍት በመስጠት፣ የተለየ የልምምድ እቅድ በማዘጋጀት እና በጥንቃቄ በመጠቀም የተለየ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ነው።
👉እንደገና የተወለደው ፍሬው ጌታሁን
በኢትዮጵያ እግርኳስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፈጣን ዕድገት እያሳዩ ከሚገኙ ግብጠባቂዎች አንዱ የሆነው ፍሬው ጌታሁን ከዓመታት በፊት ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ አርሲ ነገሌ አስደናቂ እምርታን በማሳየት ከሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች አንዱ ለሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን ለማኖር በቅቷል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኃላም በአዲስ አበባ ከተማ በነበረው ቆይታ በቂ የመሰለፍ ዕድልን ያገኝ ያልነበረው ተጫዋቹ በድሬዳዋ ከተማ ግን እንደ አዲስ የተወለደ ይመስላል። ዓምና ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ከሳምሶን አሰፋ ጋር በመቀያየር ሲሰለፍ የነበረው ፍሬው ዘንድሮ አንጋፋው ግብ ጠባቂ ከክለቡ መልቀቁን ተከትሎ ቁጥር አንድነቱን ያለ ተቀናቃኝ በመያዝ የሊግ ጨዋታዎች ማድረግ ጀምሯል። ይህን ተከትሎ የራስ መተማመኑ እየጨመረ የሚገኘው ግብ ጠባቂው በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር ቢወጣም በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከመዲናይቱ ኃያላን ክለቦች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት ግቦችን ቢያስረናግድም ፍፁም ቅጣት ምትን ከማዳን አልፎ በርካታ ጥሩ ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን ግብ ከመሆን እየታደገ ይገኛል። በሊጉ ከሚገኙ አመዛኞቹ ግብ ጠባቂዎች በተለየ ጠንቃቃ እና ስህተት የማይሰራ መሆኑም እዚህ ጋር መጠቀስ የሚኖርበት ነው። በዚህም ምክንያት በሦስተኛው ሳምንት የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን ውስጥ በተጠባባቂነት ትይዟል።
👉መሐመድ ሙንታሪ “ምነው አለ ?”
ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን 3-1 በረታበት ጨዋታ መሐመድ መንታሪ ቀጥታ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
ቀይ ማየት የሚያስገርም ጉዳይ ባይሆንም ያለምክንያት ሲሆን ግን አነጋጋሪያ መሆኑ አይቀርም። መቼም እግርኳስ ነውና ተጫዋቾች ስሜታዊ ቢሆኑ ከምክንያታዊነት ቢርቁም ላይፈረድባቸው ይችላል። ግን ደግሞ ቡድኑ 3-0 እየመራ ጨዋታውም እየተገባደደ ባለበት ሰዓት ላይ አንድ ግብ ሲቆጠርበት ተጋጣሚ ደስታውን ለመግለፅ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ከሜዳ መወገድ በስሜታዊነት ብቻ የሚታለፍ አይደለም።
እንዲህ ዓይነት አላስፈላጊ ጀብደኝነት ቡድንን በዛው ጨዋታ ቀሪ ደቂቃዎች ጭንቀት ላይ ከመጣል ባለፈ ለቀጣይ ሦስት ጨዋታዎች ጉድለት እንዲፈጠርበት የሚያደርግ መሆኑ የዛሬውን የሙንታሪን ተግባር ስናይ ‘ምን ነክቶት ነው ?’ ብለን ለመጠየቅ ተገደናል።
👉የግርማ በቀለና የተስፋዬ አለባቸው ሽኩቻ
በትናንቱ የሲዳማ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በተቃራኒ የተሰለፉት የሲዳማ ቡናው አምበል ግርማ በቀለና የሀዲያ ሆሳዕናው አማካይ ተስፋዬ አለባቸው በረባ ባረባው ሲነታረኩ ብሎም በጨዋታው በበርካታ አጋጣሚዎች ሲጎሻሙና ሲጎነታተሉ ተስተውሏል።
ሁለቱ ለካርድ ቅርብ የሆኑ እና በሊጉ ከሚጠቀሱ ኃይልን የቀላቀለ አጨዋወት መገለጫቸው የሆኑት ተጫዋቾች ይህ ባህሪያቸው ለተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ምቾት የማይሰጥ ቢሆንም በትናንቱ ጨዋታ ሲያስመለክቱን የነበረው ድርጊት ቡድናቸውን በምንም መለኪያ ሊጠቅም የማይችል ተግባር ነበር።
ተጫዋቾቹ ይባስ ብሎ በመጀመሪያው አጋማሽ በአንድ አጋጣሚ ለያዥ ለገላጋይ አስቸግረው ለፀብ ሲገባበዙ ተስተውሏል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታው የቴሌቪዥን ሽፋን ባለማግኘቱ ሁነቱ በስታዲየም የተገኙ ግለሰቦች ብቻ ትውስታ ሆኖ ቀረ እንጂ ከዚህ በላይም ባነጋገረ ነበር።
👉በቀይ ካርድ ለመውጣት የጓጉ የሚመስሉት አንዳንድ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች
ድሬዳዋ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ ምንም እንኳ በግልፅ የታዩ የዳኝነት ስህተቶች የነበሩ ቢሆንም ለክስተቶቹ የድሬዳዋ ከተማ አንዳንድ ተጫዋቾች ያሳዩት ግብረመልስ ግን በትልቅ ደረጃ ከሚጫወቱ የሙሉ ሰዓት እግርኳስ ተጫዋቾች የሚጠበቅ አልነበረም።
በማያጠያይቅ መልኩ የዳኝነት ውሳኔዎቹ የጨዋታውን አጠቃላይ መልክ የቀየሩ ቢሆንም ተጫዋቾች በስነ ልቦና ረገድ መዘጋጀት የሚኖርባቸው ነገሮች በሙሉ ከቡድናቸው በተቃራኒ ሁኔታ በሚጓዙበት ወቅትም እንኳን ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ከጨዋታው አንዳች በጎ ውጤትን ይዞ ስለመውጣት መሆን ሲገባው አንዳንድ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች በተለይም በ55ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ቡና ካስቆጠራት ፍፁም ቅጣት ምት መልስ ሜዳ ላይ ያደርጉት የነበረው ድርጊት የተገባ አልነበረም።
ኃላ ላይ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጡት ዳንኤል ደምሴና በረከት ሳሙኤልን ጨምሮ ፍቃዱ ደነቀም የጨዋታውን ውጤት ለመቀልበስ ከመታተር ይልቅ በተጋጣሚ ተጫዋቾች ላይ እጅግ አደገኛ የነበሩ ጥፋቶችን ሲፈፅም ተስተውሏል። በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወጡም የነበራቸው ስሜት ለሀሳባችን ማጠናከርያነት መዋል የሚችሉ ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ