ኢትዮጵያ ቡና እና ቡና ባንክ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል።
ስምምነቱን አስመልክቶ በፅሁፍ የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን ይመስላል።
በባለአክሲዮን ብዛት ከቀዳሚ ባንኮች ተርታ የሚመደበው ቡና ባንክ እና በደጋፊ ቁጥር ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የዘላቂ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ።
ሁለቱ “ቡናዎች” በሁሉም ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት ተፈራርመው ወደስራ መግባታቸውን ይፋ ያደረጉት ዛሬ በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው ባንኩም ሆነ ክለቡ የሚጋሩት ስም የሁሉም ኢትዮጲያዊ ከመሆኑ ባሻገር ህዝባዊ መሰረት ያላቸው መሆናቸው አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ መለያቸው ነው ተብሏል።
ስምምነቱ የተፈረመው በባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ እና በክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ሲሆን በስነስርዓቱ ላይ የባንኩና የክለቡ የስራ አመራር አባላት ተገኝተዋል። በስምምነቱ መሰረትም ቡና ባንክ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የ 5 ሚሊዮን ብር የአንድ አመት ስፖንሰርሺፕ ክፍያ የሚከፍል ሲሆን ስምምንቱም በየዓመቱ የሚታደስ ይህናል።
በስምምነቱ መሰረት ክለቡ የባንኩን አርማ በተጫዋቾች ቲሸርትና ቁምጣ ላይ በማሳየት ባንኩን ያስተዋውቃል፡፡በተጨማሪም በሜዳውም ይሁን ያለሜዳው ጨዋታ በሚኖረው ወቅት የባንኩ ቢልቦርድ ማስታወቂያ በጨዋታው ሜዳ አካባቢ እንዲቀመጥ ያደርጋል። ክለቡ በተቻለው መጠን የባንኩን ብራንድ እና አገልግሎቶች እንዲያስተዋውቅም በስምምነቱ ተካትቷል።
ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪ የስፖርት ክለቡ የባንክ ሂሳቡን በባንኩ እንዲከፍት ከማድረግ ጀምሮ የክለቡ አባላትና ደጋፊዎች የባንኩ ደንበኛ እንዲሆኑ ማድረግን የመሳሰሉ የባንክ አገልግሎቶችን ከባንኩ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
እንደስምምነቱ ባንኩ የስፖርት ክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ወርሃዊ የአባልነት መዋጮአቸውን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር በመታገዝ በባንኩ በኩል እንዲከፍሉ የሚያስችላቸው አሰራር ይዘረጋል። በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ የክለቡ አባላትም የባንክ አገልግሎት እገዛ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ቡና ባንክና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እንደስማቸው አንድ መሆን የጋራ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ሌሎች በርካታ ስራዎችንም በጥምረት ለመስራት መስማማታቸውን ነው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያበሰሩት፡፡
ከተመሰረተ 11 ዓመታት የሆነውና ከ13ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ቡና ባንክ የእግር ኳስ ስፖርቱን በመደገፍና በዓለም አደባባይ አርማውን በማስተዋወቅ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተሰለፈ
ባንክ ሆኗል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ