ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዕውነታዎች እና ቁጥሮች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎችን እነሆ!

– በዚህ ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 19 ጎሎች ተቆጥረዋል። ሦስት ጎሎች በጨዋታ በአማካይ የተቆጠሩበት የዚህ ሳምንት ካለፈው በአራት ከፍ ያለ የጎል መጠን አስመዝግቧል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማ ብቸኛው ጎል ሳያስቆጥር የወጣ ቡድን ሲሆን ሌሎቹ ክለቦች ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ በሦስት ጎሎች በርካታ ጎሎችን ያስቆጠሩ ቡድኖች ሆነዋል።

– ከ19 የሳምንቱ ጎሎች መካከል አራት ጎሎች (ሙጂብ፣ ምንይሉ፣ ዳዊት እና ዳዋ) በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥሩ፤ ሁለት ኳሶች (ሞኞት በራሱ ላይ እና አስቻለው) ከቅጣት ምት የተነሳ ኳስ አስቆጥረዋል። ሁለት ጎሎች ደግሞ (አይዛክ እና ምኞት) ከማዕዘን ምት የተነሱ ኳሶች አስቆጥረዋል። ቀሪዎቹ አስራ አንድ ጎሎች በክፍት ጨዋታ የተመዘገቡ ናቸው።

– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት አስራ ዘጠኙም ጎሎች በእግር ተመትተው የተቆጠሩ ሲሆን ይህም በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

– ሀብታሙ ታደሰ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ጎል በሳምንቱ ከሳጥን ውጪ ተመትቶ የተቆጠረ ብቸኛ ጎል ነው።

– በዚህ ሳምንት ጎሎች ላይ 17 ተጫዋቾች ድርሻ የነበራቸው ሲሆን ምኞት ለራሱ እና ለተጋጣሚ እንዲሁም ከአቡበከር ናስር ውጪ ሌሎቹ አንድ አንድ አስቆጥረዋል።

– በተቆጠሩ ጎሎች ላይ ዘጠኝ ተጫዋቾች በማመቻቸት ተሳትፎ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ፣ ሳሊፉ ፎፋና እና ሀብታሙ ታደሰ ጎል እና አሲስት ያስመዘገቡ ተጫዋቾች ሆነዋል።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች 23 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ ሁለት የቀይ ካርዶች ታይተዋል።

– የሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በስምንት ካርዶች ከፍተኛውን ቁጥር ይዟል።

– ባህር ዳር ከተማ ሁለት ቀይ እና አምስት ቢጫ በማስመዝገብ ቀዳሚው ቡድን ሆኗል።

– በሳምንቱ የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ቡና ከ ሰበታ (በዓምላክ ተሰማ) እና ጅማ ከ ሀዋሳ (ኢያሱ ፈንቴ) ምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳይመዙ ጨዋታው ተጠናቋል። ይህም በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ዕውነታዎች

– ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ከዚህ ቀደም ካሸነፈው የጨዋታ ቁጥር ጋር እኩል የሆነ ድል አስመዝግቧል። በ2008 አንድ፣ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች አሸንፎ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ገና በአራት ጨዋታ አራቱንም አሸንፏል።

– የሀዋሳ ከተማው ምኞት ደበበ አዲስ ሁነት አስመዝግቧል። በ88ኛው ደቂቃ ራሱ ላይ ጎል ያስቆጠረው ምኞት በጭማሪ ደቂቃ ለቡዱኑ የአቻነት ጎል አስቆጥሯል።

– የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል በቀጥታ ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል የለጋው ኳስ እስራኤል እሸቱ ጋር ደርሶ አጥቂው ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል። በዚህም በውድድር ዓመቱ ለጎል ያመቻቸ የመጀመርያው ግብ ጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል።

– የሰበታ ከተማው አጥቂ ቃልኪዳን ዘላለም ተቀይሮ በገባ 30 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ በመጀመርያ ንከኪው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጎል አስቆጥሯል።

– የድሬዳዋ ከተማው አስቻለው ግርማ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ቀጥተኛ የጎል ተሳትፎ አድርጓል። የመስመር ተጫዋቹ እስካሁን ሁለት ጎሎች እና ሁለት አሲስት በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።

– ባህር ዳር ከተማ በአንድ ጨዋታ ሁለት ቀይ ካርድ ያስመዘገበ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ቡድን ሆኗል። ድሬዳዋ ከተማ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁለት ቀይ ካርዶች አስመዝግቧል።
– ሀዲያ ሆሳዕና መቶ በመቶ ውጤት በማስመዝገብ ብቸኛው የሊጉ ቡድን ነው። ነብሮቹ ከአራት ጨዋታ አራት ድል አስመዝግበዋል።

– ወልቂጤ ከተማ የዓመቱን የመጀመርያ ሽንፈት ሲቀምስ በተቃራኒው ወልቂጤን ያሸነፈው ሲዳማ ቡና የዓመቱን የመጀመርያ ድል አጣጥሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ