ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ ቀን የሚከፈትበትን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

የመጀመሪያ የሊግ ድሉን ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገባው ድሬዳዋ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ መጠነኛ መነቃቃት ቢታይበትም ከአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ ጋር ተደምሮ የፈለገውን ውጤት ሳያሳካ ቀርቷል። የዚያ ጨዋታ መዘዝ ሁለት ተጫዋቾቹን ያሳጣው መሆኑም በነገው ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ እንዲኖረው ሆኗል። በእርግጥ በንፅፅር ቀለል ከሚል ተጋጣሚ ጋር የሚገናኝ መሆኑ የሚፈጠርበትን ክፍተት በመሸፈን አጥቅቶ ለመጫወት እንደሚሞክር ይጠበቃል። ወሳኝ አጥቅዎቹን ግልጋሎት የሚያገኘው ድሬዳዋ ከአማካይ ክፍሉ ከቀደሙት ጨዋታዎች የተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ከፊት መስመሩም የተሻሻለ የአጨራረስ ብቃት የሚጠብቅ ይሆናል። በማጥቃቱ ረገድ ከተጋጣሚው የኃላ መስመር ጀርባ ፈጣኖቹ አጥቂዎቹ የሚፈልጉትን ዓይነት ክፍተት የማያገኝ ከሆነ በቅብብሎች ክፍተቶችን ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት ላይ ብዙ ጊዜ እንዲወስድ ሊገደድ ይችላል። በዋነኝነት ግን ከአማካይ ክፍሉ የሚነሱ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች የሙከራ ምንጮቹ ሊሆኑ ይችላሉ። በጨዋታው ድሬዳዋዎች ያለ በቂ ልምምድ ጨዋታ በማድረጉ ተቀይሮ የወጣው ኢታሙና ኬይሙኒ ፣ የኮሮና ምርመራ ባለማድረጉ የቡናው ጨዋታ ያመለጠው ረመዳን ናስር እና ጉዳት ላይ የከረመው ሪችሞንድ አዶንጎን ከጉዳት መልስ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። በተቃራኒው በቡናው ጨዋታ በቀይ የወጡት በረከት ሳሙኤል እና ዳንኤል ደምሴን በቅጣት ይጣል።

እንደተጋጣሙው ሀሉ የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ የሚገባው ጅማ አባ ጅፋር በፋሲል ከነማ ከደረሰበት ሽንፈት ማግስት ድሬዳዋን ያገኛል። በመከላከል ረገድ ለተጋጣሚዎቹ ሰፊ የመሮጫ ክፍተትን ሲተው የታየው ቡድኑ በነገው ጨዋታ በተለይም ግብ ማስቆጠር ከቻለ መሰል ክፍተቶችን ለመድፈን እንደሚሞክር ይጠበቃል። ያ የማይሆን ከሆነ ግን ለድሬዳዋ የፊት አጥቂዎች ነገሮች ቀላል ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። በማጥቃቱ በኩል በቂ የግብ ዕድሎችን ለፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ማቅረብ ሲሳነው የሚታየው ጅማ በነገው ጨዋታ ቀጥተኛ የሆኑ ኳሶችን ወደ ፊት ለማሳለፍ እንደሚሞክር ይጠበቃል። ከሁሉም በላይ ከባድ የሚሆነው ግን ቡድኑ ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች መነሻነት በሚፈጠር የተነሳሽነት ማነስ ሜዳ ውስጥ እንዳይቸገር በማድረግ ከጨዋታው ነጥብ ለማግኘት እስከመጨረሻው እንዲለፋ ማድረጉ ላይ ነው። ይህ ኃላፊነት የተጣለባቸው የአሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ቡድን ከጉዳት ያላገገመው ከድር ኸይረዲንን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ቅጣት ላይ የሚገኘው ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪም ከጨዋታው ውጪ ነው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ድሬ እና ጅማ ከአራት ግንኙነታቸው በአንዱ ብቻ አቻ በተለያዩበት ታሪካቸው ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ ጅማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

– በአራቱ ጨዋታዎች ድሬዎች ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ጅማዎች ደግሞ አራት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

ምንያምር ጴጥሮስ – ፍቃዱ ደነቀ – ፍሬዘር ካሳ – ዘነበ ከበደ

አስጨናቂ ሉቃስ – ኤልያስ ማሞ

ጁኒያስ ናንጂቡ – ኢታሙና ኬይሙኒ – አስቻለው ግርማ

ሪቻርድ ኦዶንጎ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ

ትርታዬ ደመቀ – ንጋቱ ገብረስላሴ – ሱራፌል ዐወል

ሳምሶን ቆልቻ – ብዙአየሁ እንዳሻው – ሳዲቅ ሴቾ


© ሶከር ኢትዮጵያ