ከረቡዕ እስከ ዓርብ በተደረጉት የሁለተኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎች እነሆ!
– በሦስተኛው ሳምንት በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 24 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ካለፉት ሁለት ሳምንታት ከፍ ያለ ሲሆን በአማካይ በጨዋታ አራት ጎሎች መቆጠር ችለዋል።
– ከአዳማ ከተማ በቀር ሁሉም ቡድኖች ጎል ማስቆጠር ሲችሉ ባህር ዳር ብቸኛው ጎል ያልተስተናገደበት ቡድን ሆኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ደግሞ አራት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግበዋል።
– ከተቆጠሩት 24 ጎሎች መካከል አንዷ በሀዋሳ ከተማው ዳዊት ታደሰ አማካኝነት በራስ የተቆጠረች ጎል ናት። ይህም በዘንድሮው የውድድር ዓመት በራስ ላይ የተቆጠረ የመጀመርያው ጎል ሆኖ ተመዝግቧል።
– የጎሎቹን መንገድ ስንመለከት አራት ጎሎች (ጌታነህ ከበደ፣ ብሩክ በየነ፣ ዘነበ ከበደ እና አማኑኤል ዮሐንስ) ከፍፁም ቅጣት ምት ሲቆጠሩ ሦስት ጎሎች (አምሳሉ ጥላሁን፣ እንድሪስ ሰዒድ እና ፍፁም ዓለሙ) ከቀጥታ ቅጣት ምት ተቆጥረዋል። ከማዕዘን ምት ከተሻማ ኳስ ሁለት (አይዛክ ኢሲንዴ እና ዳዊት ታደሰ ራሱ ላይ)፣ መነሻቸው ከቅጣት ምት ከሆኑ ኳሶች ሁለት (ቢስማርክ አፒያ እና ጊት ጋትኮች) ጎሎች ተቆጥረዋል። ሌሎቹ 13 ጎሎች የተቆጠሩት ከክፍት ጨዋታ ነው።
– በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች መካከል 21 በእግር ተመትተው የተቆጠሩ ሲሆን ሦስት ብቻ (ጌታነህ፣ ኢሲንዴ እና ባዬ) በግንባር በመግጨት አስቆጥረዋል።
– ከ24 ጎሎች መካከል አራት ጎሎች ከሳጥን ውጪ ሲቆጠሩ ከላይ ከተገለፁት የቅጣት ምት ጎሎች በተቃራኒ በክፍት ጨዋታ ከሳጥን ውጪ ጎል ያስቆጠረው የወልቂጤው ያሬድ ታደሰ ብቻ ነው። ሌሎቹ ሃያ ጎሎች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ተቆጥረዋል።
– 21 ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ላይ ተሳትፎ አድርገዋል። (አንዱ በራስ ላይ የተቆጠረ ነው) ጌታነህ ከበደ፣ ያሬድ ታደሰ እና ሀብታሙ ታደሰ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥሩ ቀሪዎቹ 18 ተጫዋቾች አንድ አንድ አስቆጥረዋል።
– በዚህ ሳምንት አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶች ሲሰጡ አራቱ ወደ ግብነት ተቀይረዋል። የቡናው ታፈሰ ሰለሞን የመታውን የድሬዳዋው ፍሬው ጌታሁን ማምከን ችሏል።
– በጎል ላይ ያለ ተሳትፎን ስንመለከት የፋሲል ከነማው ሽመክት ጉግሳ ቡድኑ ባስቆጠራቸው አራቱም ጎሎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል። (አንድ አስቆጠረ፣ ሁለት አመቻቸ፣ አንድ ለተቆጠረ ቅጣት ምት መሰጠት ምክንያት ሆነ)። በተመሳሳይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለውም ቡድኑ ባስቆጠራቸው አራቱም ጎሎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል። (ሁለት አቀበለ፣ አንድ ራስ ላይ የተቆጠረ ጎል አሻማ፣ ፍ/ቅ/ም አስገኘ)
– 15 ተጫዋቾች በቀጥታ ጎል የሆነ ኳስ በማመቻቸት ተሳትፎ አድርገዋል። የሀዲያ ሆሳዕናው አልሀሰን ካሉሻ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው፣ የኢትዮጵያ ቡናው አሥራት ቱንጆ እና የፋሲል ከነማው ሽመክት ጉግሳ ሁለት ኳስ በማመቻቸት ቀዳሚ ናቸው።
– በዚህ ሳምንት በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች 29 የማስጠንቀቂያ እና 3 የቀይ ካርዶች ተመዘዋል። ይህም ካለፈው ሳምንት በአምሰት ቢጫ ከፍ ያለ ሲሆን በቀይ ካርድ ረገድ ካለፈው ጋር ተመሳሳይ ነው።
– የቡና እና ድሬዳዋ ጨዋታ አምስት ቢጫ እና ሁለት ቀይ ካርድ ተመዞበት የሳምንቱን በርካታ ቁጥር ሲያስመዘገብ ድሬዳዋ በሦስት ቢጫ እና ሁለት ቀይ ካርድ ከፍተኛ ካርድ ያስተናገደ ክለብ ሆኗል።
ዕውነታዎች
– ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ እጅግ ግሩም አጀማመርን አሳይቷል። ከሦስት ጨዋታ ሙሉ ዘጠኝ ነጥቦች ያሳካው ቡድኑ ከወዲሁ የሰበሰበው ነጥብ ከዚህ ቀደም በተሳተፈበት የ2008 የውድድር ዓመት በአጠቃላይ (በ26 ጨዋታ) ከሰበሰበው ስምንት ነጥብ በአንድ ብልጫ ያለው ነው። በተሰረዘው የዓምናው የውድድር ዓመት በ17 ጨዋታ ከሰበሰበው 14 ነጥብ ላይ ለመድረስም አምስት ነጥቦች ብቻ ቀርቶታል። በተጨማሪም በሁለቱ የውድድር ዓመታት ግርጌ ላይ ሆኖ ወደ ላይ ሲመለከት የነበረው ቡድን አሁን ከአናት ሆኖ ሌሎችን ወደ ታች መመልከት ጀምሯል።
– የሀብታሙ ታደሰ ክንድ በድሬዳዋ ቡድኖች ላይ በርትቷል። ተጫዋቹ በከፍተኛ ሊግ ለወልቂጤ በሚጫወትበት ወቅት በ2011 ቡድኑ ናሽናል ሲሜንትን 7-2 ሲያሸንፍ ስድስት ጎሎች በማስቆጠር የሊጉ ብቸኛ ባለታሪክ መሆን የቻለ ሲሆን በዛው ዓመት በመጀመርያው ዙር 7-1 ሲያሸንፉም ሐት-ትሪክ መስራት ችሎ ነበር። በ2010 ወልቂጤዎች ናሽናል ሴሜንትን 6-0 ሲያሸንፉ ሁለት ጎል በስሙ ያስመዘገበ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ሁለት ጎሎች አስቆጥሯል። በረቡዑ ጨዋታ ድሬራዋ ከተማ ላይ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሩን ተከትሎም በድሬዳዋ ቡድኖች ላይ ያስቆጠረውን ጎል ብዛት አስራ ሦስት አድርሶታል።
– የሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከተከታታይ የጎል ድርቅ በኋላ በአምስት ጎሎች ረስርሷል። የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ጨምሮ በሊጉ ያለፉ ሦስት ግንኙነታቸውን ያለ ጎል በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በተጨማሪም የብሩክ በየነ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሀዋሳ ከአራት ጨዋታ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያስቆጠረው የመጀመርያ ጎል ሆኖ ተመዝግቧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ