ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ በመሳይ ተመስገን አስደናቂ ብቃት ታግዞ አርባምንጭን ረትቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በግብ ተንበሽብሽቦ አርባምንጭ ከተማን 7 ለ 0 ረምርሟል፡፡

ሀዋሳዎች ካለፈው ስህተታቸው ተምረው መሐል ሜዳው ላይ በሰሩት አስደናቂ ጥምረት ነበር ገና በጊዜ ጎል ወደ ማስቆጠሩ የገቡት። 7ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት መና ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ሰጥታት በግራ መስመር ተሰልፋ ለአርባምንጮች ፈተና የነበረችው መሳይ ተመስገን በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጣው ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች። 

ገና አንድ ግብ በጊዜ ለማስተናገድ የተገደዱት አርባምንጭ ከተማዎች ያገኙትን ኳስ በቅብብሎሽ ሂደት ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በረጅሙ ካገኙበት ቦታ መምታት አልያም ከቅጣት ምት ሙከራን ቢያደርጉም የተሳካ ግን አልነበረም። በተቃራኒው ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል በመድረሱ የተዋጣላቸው ሀዋሳዎች ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ 14ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ለሀዋሳ ተሰልፋ በመጫወት ለመሐል ሜዳው ሚዛን ስትሰጥ የነበረችው ዙፋን ደፈርሻ ከማዕዘን ስታሻማ ተከላካይዋ ትዝታ ኃይለሚካኤል በግንባር በመግጨት አስቆጥራ የሀዋሳን የጎል መጠን አሳድጋለች፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ረድኤት አስረሳኸኝ በግል ጥረቷ ኳስን ይዛ ወደ ሳጥን በመግባት ሦስተኛ ግብ አክላለች፡፡ 17ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አስረሳኸኝ ከመሐል ሜዳው አጋማሽ የለቀቀችውን ኳስ ነፃነት መና ወደ ግብነት ለውጣው የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ አራት አሳድጋለች፡፡

አርባምንጮች በፍጥነት አንጋፋዋ አጥቂ ሰናይት ባሩዳን ቀይረው ቢያስገቡም ተጫዋቿ በግሏ ከምታደርገው ጥረት ውጪ ሊረዷት የሚችሉ አጋዥ ተጫዋቾች ባለመኖራቸው ሜዳ ላይ ስትባክን እንዲሁም በቀላሉ በሀዋሳ ተከላካዮች ስትነጠቅ አስተውለናል፡፡

በተደጋጋሚ ለአርባምንጭ ተከላካዮች ፈተና ሆና የዋለችው መሳይ ተመስገን ከዓይናለም አደራ በቀኝ በኩል ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጣ ለራሷ ሁለተኛ ሀዋሳን ደግሞ ወደ 5 ለ 0 በማሸጋገር ወደ መልበሻ ክፍል አአሳድጋለች፡፡

ከእረፍት መልስ አርባምንጮች ኳስን ይዞ ለመጫወት ቢሞክሩም ወጥነት ያለው ካለመሆኑ የተነሳ የኳሳቸው የመጨረሻ ማረፊያ ውጤታማ አደለም በአንፃሩ በዚህኛው አጋማሽ ከመሐል ክፍሉ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶችን በሁለቱም ኮሪደር በመጣል ሀዋሳዎች ሌላ ግብ ለማስቆጠር አሁንም ጥረት አልተለያቸውም።

49ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ አጥቂ መሳይ ተመስገን እና የአርባምንጯ አምበል ድርሻዬ መንዛ መሀል ሜዳ አካባቢ ዕርስ በዕርስ ተጋጭተው ጉዳት አስተናግደው የወደቁ ሲሆን መሳይ በተደረገላት ህክምና ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሳ መጫወት ስትችል የአርባምንጯ አምበል ድርሻዬ ጉዳቷ ጠንከር ያለ በመሆኑ በአፋጣኝ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አምርታለች፡፡

መሳይ ወደ ሜዳ ከተመለሰች ስድስት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ከመስመር የተሻገረን ኳስ ረድኤት በግንባር ጨርፋ ስታቀብላት መሳይ ወደ ጎልነት በመለወጥ ለራሷ ሀትሪክ ስትሰራ ለሀዋሳ ስድስተኛ ጎሏን ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ከግቧ በኃላ በመልሶ ማጥቃት አርባምንጮች ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን ዕድል በሰርካለም ባሳ አማካኝነት ቢያገኙም በአጠቃቀም ድክመት አልተጠቀሙበትም፡፡

ተቀይራ በገባችው ቅድስት ቴካ እና መሳይ ተመስገን አሁንም ወደ ጎል ማነፍነፋቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች 79ኛው ደቂቃ በመሳይ ተመስገን ግብ ጨዋታውን አጠናቀዋል፡፡ በጨዋታውም መሳይ አራተኛ ግቧን ስታስቆጥር ሀዋሳም 7 ለ 0 ረምርሟል፡፡ አርባምንጭ ከተማ በሶስት ጨዋታ አስራ ሰባት ግቦችን ያስተናገደ ብቸኛ ክለብም ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለሀዋሳ አራት ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈችው መሳይ ተመስገን የልሳን የሴቶች ስፖርት ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ