የሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።
ደካማ የውድድር አጀማመር ያደረጉት አዳማ እና ሲዳማ የሚገናኙበት ጨዋታ የአንዳቸውን የሊግ ጉዞ የማቃናት ዕድልን ይዞ ነገን ይጠብቃል። በባህርዳር ሽንፈት ያስተናገደው አዳማ ከተማ በጨዋታ መጀመሪያ ላይ የሚታይበት አለመረጋጋት እና የሚቆጠሩበት ግቦች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ጨዋታውን በማሳደድ እንዲጨርስ እያደረጉት ይገኛሉ። ይህም አማካይ ክፍል ላይ በእርጋታ ቅብብሎችን ከውኖ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተፈጠሩትን ጥቂት ዕድሎችም ወደ ግብ ለመቀየር ፈተና እንዲሆንበት መንስኤ ሆኗል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ የሲዳማ የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴን ተቆጣጥሮ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ምት ካልገባ እና በቶሎ ለጥቃት ከተጋለጠ ያለፉት ጨዋታዎች እጣ እንዳይደርሰው ያሰጋል። ከዚህ ባለፈም በቀጥተኛ ኳሶች ግብ ላይ ለመድረስ እንኳን የፊት መስመሩ ግርማሞገስ ማጣት ለተጋጣሚዎች ቀላል እያደረገው ይገኛል። የነገው ተጋጣሚው በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደ መሆኑ ሲታሰብ ግን የአዳማ የአጥቂ ክፍል ጨዋታውን ራሱን ለማንቃት ሊጠቀምበት ዕድሉ እንዳለው መገመት ይቻላል።
ለአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ጥሩ ያልሆነው ዜና ግን ተስፋ የሚጥሉበት አጥቂያቸው አብዲሳ ጀማል ከጉዳት አለመመለስ ሲሆን ባለፈው ጨዋታ ከረጅም ጉዳት በኋላ ተቀይሮ የገባው ሱለይማን መሀመድ እና ፍሰሀ ቶማስም ጉዳት ላይ እንዳልሆኑ ሰምተናል።
ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ምንም ነጥብ ያላሳካው ሲዳማ ቡና በንፅፅር ቀለል ያለ ተጋጣሚ የሚያገኝ መሆኑ የቀደመ በራስ መተማመኑን ለማግኘት የሚረዳው ነው። ከኋላ የትኩረት ማነስ እና ፈጣን አጥቂዎችን የመቆጣጠር ችግር የሚታይበት ሲዳማ አማካይ ክፍሉም የተጋጣሚን የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ገትቶ ለራሱ ክፍተቶችን መፍጠር ከብዶት ይታያል። የቡድኑ ዋነኛ የፈጣራ ምንጭ ሆኖ የሚታየው ዳዊት ተፈራ እንቅስቃሴ ሲገታ ቡድኑ ለማጥቃት ሲቸገር የፊት መስመር ተሰላፊዎቹም የግብ አግቢነት መንፈስ ውስጥ ባለመሆናቸው እርጋታ ጎሏቸው ይታያሉ። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በሀዲያው ጨዋታ የዉጪ ዜጋ ተጫዋቾቻቸውን አለመጠቀማቸው እንደጎዳቸው መናገራቸው ሲታሰብ ደግሞ ቡድኑ እስካሁን እየተጠቀመበት ባለው አሰላለፍ እንደማይቀጥል እና የተለየ መልክ ኖሮት እንዳሚቀጥል ፍንጭ ይሰጣል። የነገው ጨዋታም መሰል ለውጦች ቡድኑን ምን ዓይነት መዋቅር ያስይዙታል የሚለውን ጥያቄ ሲመልስልን ከዚህ በኃላ የሚኖረው ሲዳማንም ሊያስመለክተን ይችላል።
ለሲዳማ መልካም በሆነው ዜና የመሐል ሜዳውን ሚዛን በመጠበቅ እና ለተከላካዩ ጥሩ ሽፈን በመስጠት እንዱሁም ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል ልዩነት ሊፈጥር የሚችለው ዮሴፍ ዮሐንስ መመለስ ሲሆን የመስመር ተከላካዩ ዮናታን ፍሰሐም ለሲዳማ ግልጋሎት እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በሌላ በኩል ጫላ ተሺታ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ከጉዳት ነፃ ያለመሆኑ እና የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን የመጠቀም ጉዳይ እስከነገ እልባት አለማግኘቱ ለሲዳማ ስጋት ሆነዋል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች 18 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሲዳማ 7 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አዳማ 5 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– 30 ጎሎች በተስተናገዱበት የሁለቱ ግንኙነት ሲዳማ 14 ሲያስቆጥር አዳማ 16 አስቆጥሯል።
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ታሪክ ጌትነት
ታፈሰ ሰረካ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ
ሙጃይድ መሀመድ – ደሳለኝ ደባሽ
ፀጋዬ ባልቻ – በቃሉ ገነነ – ጀሚል ያዕቆብ
የኋላእሸት ፍቃዱ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
መሳይ አያኖ
ዮናታን ፍሰሐ – ግርማ በቀለ – ፈቱዲን ጀማል – ግሩም አሰፋ
ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየሁ ዮሐንስ
ይገዙ ቦጋለ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ