ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

አራተኛው የጨዋታ ሳምንት በተጀመረበት የዛሬ ረፋዱ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከታማን 4-2 አሸንፏል።

ሰበታ ከተማ በሁለተኛው ሳምንት ሀዋሳን ካሸነፈበት ጨዋታ አሰላለፍ ውስጥ መሳይ ጳውሎስ እና ቢያድግልኝ ኤልያስን በአንተነህ ተስፋዬ እና እስራኤል እሸቱ ተክቷል። በተመሳሳይ ሀዋሳን ገጥመው የነበሩት ጊዮርጊሶች ከጉዳት የተመለሰው አስቻለው ታመነን በአብዱልከሪም መሀመድ ምትክ አሰልፈዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ አብዛኛው ደቂቃዎች መሐል ሜዳ ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች ያለፉ ነበሩ። አነስተኛ ሙከራዎች የታዩበት እና በተደደጋጋሚ የአርቢትሩ ፊሽካ ይሰማ በነበረበት በዚሁ አጋማሽ 23ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ኃይለሚካኤል አደፍርስ በእጁ በመንካቱ በተገኘ ፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ጎል አስቆጥሯል። ከግቡ ውጪ ጊዮርጊሶች በ6ኛው ደቂቃ በአዲስ ግደይ እንዲሁም በ27ኛው ደቂቃ በሮቢን ንጋላንዴ ፋሲል ገብረሚካኤልን እምብዛም ያልፈተኑ ሙከራዎች አድርገዋል። ቀዳዳዎችን በመፈለግ በጎንዮሽ ኳሶች ብዙውን ጊዜ ያሳለፉት ሰበታዎች አልፎ አልፎ ሳጥኑ አቅራቢያ አፈትልከው ለመግባት ከሚጥሩት ቡልቻ ሹራ እና እስራኤል እሸቱ እንቅስቃሴ ውጪ ተጋጣሚያቸውን ሲያስጨንቁ አልታዩም። 44ኛው ደቂቃ አዲሱ ተስፋዬ ከዳዊት እስጢፋኖስ ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን እና በፓትሪክ ማታሲ የተመለሰው ሙከራም የቡድኑ ብቸኛ የጠራ የግብ አጋጣሚ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ነቃ ብለው የገቡት ሰበታዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ከታደለ መንገሻ የተቀበለውን ኳስ ከማታሲ ጋር አንድ ለአንድ ከመረብ ያሳረፈው እስራኤል እሸቱ ነበር። ፈጣኑ አጥቂ ከሦስት ደቂቃዎች በኃላም ቡልቻ የሰጠውን ኳስ ለማስቆጠር ተቃርቦ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። ነገር ግን የጊዮርጊሶች ምላሽ ፈጣን ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ በሰበታዎች የግብ ክልል አዲሱ ወደፊት ለማቀበል ሲሞክር ጌታነህ ያቋረጠው አቤል ያለው ጋር ደርሶ አቤል በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ሲያስቆጥር ከሁለተኛ ደቂቃዎች በኃላ ከፉዓድ ፈረጃ ከተነጠቀ እና ከጌታነህ በተጀመረ መልሶ ማጥቃት አቤል ከቀኝ መስማር ያሻማውን ተቀይሮ የገባው ጋዲሳ መብራቴ በፋሲል ገ/ሚካኤል መረብ ላይ አሳርፏል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ጌታነህ ከኃላ የተላከለትን ኳስ ይዞ ከሰበታ ተከላካዮች ጋር በመታገል አራተኛ ጎል አድርጎታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ሰበታዎች ሁለተኛውን ግብ 75ኛው ደቂቃ ላይ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። ሆኖም ኃይለሚካኤል ከመስመር ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ቃልኪዳን ዘላለም ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ስቶታል። ያም ቢሆን በመጨረሻ ደቂቃ ሌላው ተቀያሪ ፍፁም ገብረማርያም ከዳዊት የተቀበለው ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ሲገባ በኤድዊን ፍሪምፖንግ ጥፋት ተሰርቶበት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ፍፁም በመምታት አስቆጥሮ ጨዋታው በጊዮርጊስ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ