የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 2-4 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በፈረሰኞቹ 4-2 አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ በኃላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ጨዋታው በገመቱት መልኩ ስለመሄዱ…

“የመጀመሪያው አጋማሽ በገመትኩት መልኩ ነበር ይሄደው። በኳስ ቁጥጥርም ጨዋታውን በመቆጣጠር የተሻልን ነበርን። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከጊዮርጊስ አማካይ ክፍል ለአጥቂዎቹ የሚላኩ ካሶችን መቆጣጠር ላይ መጠነኛ ክፍተት ነበረብን። እንዲሁም ተከላካዮቻችን የእነሱን አጥቂዎች ጀርባ ማየት አለመቻላቸው ዋጋ አስከፍሎናን። ስለዚህ ይሄንን በቀጣይ ጨዋታ አርመን ለመቅረብ ተግተን እንሰራለን።”

ስለሁለተኛው አጋማሽ የቡድኑ እንቅስቃሴ…

“ግቡን ካገባን በኋላ የኛ ተጫዋቾች ተጨማሪ ግብ ለማግባት በጉጉት የራስን ሜዳ ነቅሎ መሄድ የተጋጣሚ ቡድን መልሶ ማጥቃት እንዲጫወት አድርጓል። ከዚህ በተረፈ በሁለቱም አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር ላይ ብዙ ችግር አልነበረብንም።”

በተከላካዮች ስህተት ስለተቆጠረው ግብ…

“የምንፈልገውን የአጨዋወት ሂደት ተከትለን ለመስራት እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች ይሰራሉ። ያም ሆኖ ግን ያንኑ የአጨዋወት መንገዳችንን አልቀየርንም። ስለዚህ በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች እንዳይሰሩ እናደርጋለን እንጂ ይሄ ስህተት ተሰርቷል ብለን የአጨዋወት ፍልስፍናችንን አንቀይርም።”

አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው…

“ዛሬ ጥሩ የቡድን እንቅስቃሴ ነበር። ከተጠባባቂነት የተነሱት ጋዲሳ ፣ ከነዓን እና የአብስራ ለቡድኑ ጉልበት ከመስጠት ባለፈ በትክክለኛው ሰዓት የታክቲክ ዲስፕሊንን ሰጥተውናል። ያም አሸናፊ አድርጎናል። ግቦቹን ያስቆጠሩት ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ የቡድን ስራ ያመጣው ውጤት ነው።”

የጋዲሳ መግባት ስለፈጠረው ተፅዕኖ…

“ጋዲሳ ብቻውን አልነበረም ፤ ከፊት ከነበሩት ከነጌታነህ ከነኤቤል ጋር የነበረው ግንኙነት የፈጠረው ነው። እርግጥ ነው ለውጥ ፈጥሯል ግን ደግሞ የሌሎቹም እርዳታ ያስፈልገው ነበር። የቡድኑ አልበገር ባይነት የተለየ ነበር። ይህንንም ይዘን ወደቀጣዩ ጨዋታ እንሄዳለን።”

በእረፍት ሰዓት ለቡድናቸው ስለሰጠት ምክር…

“ኳሱን መያዝ እና መረጋጋት እንዳለባቸው ነው። ዕድል የሚፈጥሩ ቅፅበቶች እንደሚመጡ እርግጠኛ ነበርን። ተጋጣሚያችን ኳሱን በመያዝ ትኩረታችንን እንድናጣ እና ክፍቶትችን እንድንፈጥር ያረግ ነበር። በመሆኑም በእርጋታ መጠበቅ እና ክፍተቶችን ጠብቀን መጠቀም ነበረብን ያንን በአግባቡ በመጠቀማችን ደስ ተሰኝቻለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ