የብሩክ በየነ ብቸኛ ጎል ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና ላይ የ1-0 አሸናፊነትን እንዲቀዳጅ አስችላለች።
በጊዮርጊሱ ሽንፈት ከተጠቀመበት ቡድን ከግማሽ በላዩ ላይ ለውጥ ያደረግው ሀዋሳ ከተማ ዳንኤል ደርቤ ፣ ላውረንስ ላርቴ ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ሄኖክ ድልቢ ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ቸርነት አውሽን አሳርፎ ምኞት ደበበ ፣ ዘነበ ከበደ ፣ ወንድምአገኝ ማዕረግ ፣ ብርሀኑ በቀለ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና ወንድምአገኝ ኃይሉን በቀዳሚነት ተጠቅሟል። ድሬዳዋ ከተማን አሸንፎ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ወንድሜነህ ደረጄ እና አቡበከር ናስርን በምንተስኖት ከበደ እና ሚኪያስ መኮንን ቦታ ተክቷል።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እጅግ የተቀዛቀዘ ነበር። ኳስን መስርተው ለመጫወት የሚሞክሩት ሁለቱ ተጋጣሚዎች በብዛት መሀል ሜዳ አንዱ የአንዱን የኳስ ፍሰት በመቋረጥ ወደ ሳጥኖቹ ጋር በማይደርስ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው አሳልፈዋል። የተጋጣሚያቸውን ከመስመር የሚነሳ ጥቃት መቆጣጠር የቻሉት እና በንፅፅር የተሻሉ የነበሩት ሀዋሳዎች ኳስ ነጥቀው በቶሎ የቡና የግብ ክልል መድረስ ሲከብዳቸው ታይቷል። 16ኛው ደቂቃ ላይ ዮሃንስ ሴጌቦ ከግራ ሳጥን ጠርዝ ላይ መትቶት ወደ ውጪ የወጣው ኳስም ብቸኛው የቡድኑ ከባድ ሙከራ ነበር።
8ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ታደሰ አማካይነት ከሳጥን ውስጥ ከተደረገው ሙከራ በኃላ ሌላ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ያልቻሉት ቡናዎችም ከራሳቸው የግብ ክልል የዘዋቸው የሚወጡት ኳሶች መሀል ሜዳ ላይ እየከሰሙ የተለየ ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ እንደመጀመሪያው የቀጠለ ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ ከኤፍሬም ዘካርያስ በተነሳ እና በጋብርኤል አህመድ በተገጨ ኳስ ቀዳሚውን ሙከራ ያደረጉት ሀዋሳዎች ቀዳሚ ያረጋቸውን ግብ ማግኘት ችለዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ከጋብሬል አህመድ በረጅሙ ወደ ቡና የግብ ክልል የተላከውን ኳስ የጎል ክልሉንለቅቆ የወጣው ተክለማርያም ሻንቆ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ብሩክ በየነ አግኝቷት ወሳኟን ግብ ከመረብ አገናኝቷል።
ከግቡ በኋላ ማፈግፈግ የጀመሩት ሀዋሳዎች ቀስ በቀስ ሙሉ ለሙሉ ከኳስ ጀርባ ሆነው የቡናን የማጥቃት መስመሮች በሙሉ ዘግተዋል። ከአደጋው ክልል በጣም ርቀው ክፍተት በመፈለግ ሲባክኑ የነበሩት ቡናዎች ያሰቡት ሳይሳካ አንድም ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ