በሀዋሳ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ዛሬ ስላገኙት ድል…
ተከታታይ ሽንፈቶችን ካስተናገድን በኋላ ነጥብ ያስፈልገን ነበር። እርግጥ ከሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ማገኘት ይከብዳል። ምንም ቢሆንም ግን በራሳችን ላይ ህልውናችንን ወስነን ነበር የመጣነው። ነጥቡ እንደሚያስፈልገን አምነን ነበር፣ ይህም ተሳክቶልናል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ስለተከተሉት የጨዋታ መንገድ…
ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ሁለት የኳስ ቅብብል ተጫውቶ ተጋጣሚን ማጥቃት የሚፈልግ ክለብ ነው። እኛም ግብ ካገባን በኋላ ያገኘነውን ነጥብ አስጠብቀን ክፍተቶቻችንን ለመድፈን ከተቻለም የተሻለ ነገር ለማግኘት አስበን ነበር ስንጫወት የነበረው። በአጠቃላይ ግን ነጥቡ ስለሚያስፈልገን አጨዋወታችንን ገድበን ተጫውተናል።
ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው…
ሀዋሳዎች መሐል ሜዳ ላይ የነበረውን ክፍተት አጥበው ነበር ሲጫወቱ የነበረው። ከዚህም መነሻነት ከእረፍት መልስ በመስመር ላይ ጥቃቶችን ለመሰንዘር አልመን ስንጫወት ነበር። በተለይም የመስመር ተከላካዮቻችንን ሀይሌ እና አስራትን ጨምሮ የመስመር ላይ እንቅስቃሴያችንን አጠናክረን ነበር። ምክንያቱም እነሱ መሐል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ስለወሰዱብን። በዚህ መንገድ ለመጫወት ብናስብም በመልሶ ማጥቃት እንደምንጠቃ እናውቅ ነበር። በዚህም ብዙ ኳሶች ወደ እኛ መጥተው ነበር። ብዙዎቹን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ብንቆጣጠርም አንድ ኳስ በተፈጠረ ስህተት ተቆጥሮብናል።
ሌላ የጨዋታ አማራጭ ስላለመጠቀማቸው…
አንድ ቡድን መሐል ላይ ተከማችቶ ሲጫወት መስመሩን ይለቅልሃል። በዚህ ደግሞ መስመሩን በመጠቀም የግብ እድል መፍጠር አልያም መስመሩን በመጠቀም መሐሉን ማስከፈት ነው የምትችለው። ሌላው አማራጭ ተጋጣሚ የተከማቸበት ቦታ ላይ ረጅም ኳሶችን መጣል ነው። ሌላ የተለየ አማራጭ ግን አይኖርም። ግን በዝግ ቦታዎች ላይ ክፍተቶችን ፈልጎ ማግኘት የተጫዋች ብቃት ይጠይቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ