ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ዛሬ 10:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ተገናኝተው 1 ለ 1 ተለያይተዋል፡፡

ፍፁም ደካማ የአጨራረስ ክፍተት በሁለቱም ክለቦች ላይ ጎልቶ በታየበት መርሀ ግብር በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎች ተገኝተው በአጥቂዎች ዝንጉነት ወደ ግብ ሳይለወጡ ሲቀሩ አስተውለናል፡፡ በተለይ የቀድሞዋ የንግድ ባንክ አጥቂ ቤተልሄም ታምሩ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች አዲስ አበባ ከተማ መሪ ሊሆን የሚችልበትን መልካም አጋጣሚ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ብታገኝም በቀላሉ ስታምክናቸው ተስተውሏል፡፡

አዳማ ከተማዎች በአንፃሩ እንደ ቡድን ከመጫወት ይልቅ ግላዊ እንቅስቃሴ ላይ በሚያዘወትሩ ተጫዋቾች በመሞላቱ ያገኟቸውን ግልፅ ዕድሎች በቀላሉ በግድየለሽነት ሲስቱ መመልከት ተችሏል፡፡ለዚህም ማሳያ ምርቃት ፈለቀ ያገኘቻቸው ሶስት ንፁህ አጋጣሚዎች አስቆጪዎች ናቸው። በተለይ 34ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ የአዲስ አበባዋ ግብ ጠባቂ ቤተልሄም ጥረት ወደ ግብነት ሳይለወጥ ቀርቷል፡፡ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ሁለት ደቂቃዎች እንደቀሩ ከማህዘን ምት የተሻማን ኳስ አልፊያ ጃርሶ አግኝታ መታው ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ከግቡ ጠርዝ ላይ እንደምንም አውጥታዋለች፡፡

ከእረፍት መልስ የነበረው የአጋማሹ የጨዋታ ሂደት ፍላጎት በተጎዳኝ የታየበት እና የበሰለ የጨዋታ መንገድን ግን ያልተመለከትንበት ነበር ለማለት ያስችላል፡፡ አዲስ አበባዎች ለሚያገኙት የመጨረሻ ዕድል አጋዥ ሌላ ተጫዋች ባለመኖሩ ያገኟቸውን ዕድሎች በጊዜ እንዳያስቆጥሩ ያደረጋቸው ምክንያቶች ነበሩ፡፡ በተለይ በአንድ ሁለት እና በተሻገሪ ኳሶች ሲሄዱበት የነበረበት ሂደት ከአዳማ ደካማው የመከላከል አጨዋወት ጋር ተዳምሮ በቀላሉ ያስቆጥራሉ ቢባልም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ በዚህ ሒደት ቤተልሄም ሰማን ብቻዋን አግኝታ አጠጋቧ ተቀባይ ተጫዋች ባለ መኖሩ ራሷ ሞክራ ስታዋለች፡፡

63ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ተቀይራ የገባችው ሰላማዊት ኃይሌ የአዳማ የተከላካይ ተጫዋቾች ስህተት ተጠቅማ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ግብ ካስተናገዱ በኃላ በመጠኑም ቢሆን ግብ ለማስቆጠር አዳማዎች ጥረዋል በተለይ ከቆሙ ኳሶች በአልፊያ እና ምርቃት አጋጣሚን ፈጥሮ አቻ ለመሆን ታትረዋል፡፡82ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የአዲስ አበባ የግብ ክልል አካባቢ የተገኘውን አጨቃጫቂ የቅጣት ምት ስትባክን ረጅሙን ደቂቃ የቆየችሁ ምርቃት ፈለቀ መታው ግብ አስቆጥራ ክለቧን አቻ አድርጋለች፡፡ ከግቧ በኃላ አዲስ አበባ ከተማዎች በእማዋይሽ ይመር የመጨረሻ ደቂቃ ሙከራ ቢያደርጉም ጨዋታው ግን 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአዲስ አበባ ከተማዋ አማካይ የውብዳር መስፍንን የጨዋታውን ምርጥ በማለት ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ