የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ የአቋም መግለጫ ሲያወጣ አላግባብ የስም ማጥፋት ዘመቻ በተቋሙ ላይ ስለመደረጉ ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ ያወጣው የአቋም መግለጫ ይህንን ይመስላል:-
የአቋም መግለጫ
ታህሳስ 19/2013ዓ.ም አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህዳር 27/2013ዓ.ም 12ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱ ይታወሳል፤ ጠቅላላ ጉባዔው ከመካሄዱ በፊት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል። ከነዚህም መካከል ለጉባዔው አባላት ጥሪ እንዲሁም የጉባዔው ሰነዶች በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ተልከዋል።
በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ የስራ አመራር ኮሚቴ ተሟልተው መገኘት ስላለባቸው ለሁሉም አባላት ጥሪ ተላልፏል። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኮ/ል አወል አብዱራሂም ጥሪ ከተደረገላቸው አባላት አንዱ ናቸው። መንግስታችን በጁንታው ኃይሎች በትግራይ ክልል እየወሰደ በነበረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ዘመቻ ወቅት የትግራይ ክልል ተወካይ የሆኑት የስራ አመራር ኮሚቴ አባል በትግራይ ክልል ይገኙ ነበር። በወቅቱ ትግራይ የነበሩ የተወሰኑ እግር ኳስ ተጫዋቾች በዩኒሴፍ በኩል ወደ አዲስ አበባ መተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ምክትል ፕሬዝዳንቱም በጉባኤ ላይ ተገኝተው የስራ ድርሻ ውን በተመለከተ በጉባዔው ለሚነሱ አስተያየቶች ምላሽ መስጠት ስላለባቸው እንደ ተጫዋቾች ሁሉ ህዳር 14/2013ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ነገር ግን አርአያ ተስፋ ማሪያም የተባለ ግለሰብ በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ የፌዴሬሽናችንን በጎ ገጽታ ግንዛቤ አልባ በሆነ አስተያየታቸው በተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማድረግ ላይ ናቸው።
እንዲሁም የባለስልጣን ልጆች ከብሔራዊ ቡድን ጋር ከሀገር እንዲወጡ ተደርጓል ያሉት አሉባልታ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ እና በማስረጃ ያልተደገፈ ወሬ መሆኑን ለህዝባችን እያሳወቅን፤ ይህ ሂደት እግር ኳሱን እና ፖለቲካውን ካለመረዳት የመጣ ጭፍን ተቋሙን የማጠልሸት እና የእኔ ብቻ አውቃልሃለው የአንድ ወገን አስተያየት ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ውጪ ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን ለህዝባችን እየገለጽን፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማስፈን እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን እርምጃ ሁሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በግንባር ቀደምነት የሚደግፍ መሆኑን እየገለጽን በተቋማችን ላይ የተከፈተብንን የስም ማጥፋት ዘመቻ በህግ አግባብ የምንጠይቅ ይሆናል።
“ክብር ኢትዮጵያ ህዝብ እና ለመከላከያ ሰራዊታችን!!
© ሶከር ኢትዮጵያ