በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሳምንት መርሀ ግብር ከሁለት ቀናት እረፍት በኃላ ዛሬ ሲጀመር መከላከያ አቃቂ ቃሊቲን 2 ለ 0 አሸንፏል፡፡
ጨዋታው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ባሉት አርባ አምስት ደቂቃዎች በመልበሻ ክፍሉ ውስጥ ጭቅጭቅ ተስተናገደበትን ክስተት መመልከት ችለናል፡፡ መከላከያም ይሁን አቃቂ ቃሊቲ ለብሰው ወደ ሜዳ ሊገቡት የነበረው መለያ አረንጓዴ በመሆኑ የዕለቱ ዳኞች አንደኛው ቡድን ሌላ ቀለም ያለው ትጥቅ አድርጎ መግባት አለበት በሚል ዕጣ በመጣል አቃቂ ቃሊቲዎች ዕጣው ደርሶባቸው እንዲለውጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሆኖም “እኛ ባለ ሜዳ ነን። ያለን ይህ መለያ ብቻ ነው።” በሚል ክርክር ውስጥ ይገባል። በዚህም መሐል ዳኞቹ “መቀየር አለባችሁ” የሚል አቋም በመያዛቸው አቃቂዎች ረጅም ደቂቃን ከፈጀ እሰጣ ገባ በኃላ ጨዋታው ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቀይ መለያን በማምጣት ወደ ሜዳ ሊገቡ ችለዋል፡፡ ጨዋታው ከተያዘለት መደበኛ ሰአት አስራአንድ ደቂቃን ዘግይቶ ጀምሯል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት የነበረ ቢሆንም የሰላ የፊት መስመርን ይዞ የገባው መከላከያ ግን የሚቀመስ አልነበረም። በማጥቃቱ ረገድ የተደራጀ ቢሆንም ግን በመከላከሉ ያሳዩት የነበረው ድክመት ለአቃቂ ቃሊቲ የመስመር አማካዮች ምቾትን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ሆኖም ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብ የሚለውጥ ሁነኛ አጥቂ ባለመኖሩ በቀላሉ ያገኙትን ተደጋጋሚ ኳሶች ሲያመክኑ ተስተውሏል፡፡መከላከያዎች የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች በፈጣን የቅብብሎሽ ሽግግር በተጋጣሚያቸው ላይ ጥቃት የሰነዘሩበት ነበር፡፡ በተለይ ልማደኛዋ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ አስረኛው ደቂቃ ላይ በክፍት የጨዋታ ሂደት ያገኘችሁን ኳስ ወደ ግብ መታ ግብ ጠባቂዋ ገነት አንተነህ መልሳባታለች፡፡ ግብ ለማስቆጠር ፈጣን የሆኑ አደጋኛ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የታዩት መከላከያዎች ጥረታቸው ሰምሮ 18ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ የአቃቂዋ አምበል ገነት ፈርዳ ኳስን ለግብ ጠባቂዋ ገነት አቀብላለሁ ብላ ኳሱን በመታችበት ወቅት ከጀርባዋ የነበረችሁ ሴናፍ ዋቁማ አፍትልካ ወታ ኳስ እና መረብን በማገናኘት ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡
ግብ ካስቆጠሩ በኃላ መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየባቸው መከላከያዎች በመከላከሉ ረገድ ከነፃነት ፀጋዬ የግል እንቅስቃሴ ውጪ ደካማ በመሆናቸው ሶስት ሙከራዎችን ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ ኪፊያ አብዱራሂም ከግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ጋር ተገናኝታ ያመከነችው እና ራሷ ኪፊያ በብልጠት መሀል ለመሀል አሾልካ ፈዛ ለዋለችሁ ትደግ ፍሰሀ ሰጥታት አጥቂዋ ያልተጠቀመችበት የሚያስቆጩ ነበሩ፡፡
ከእረፍት መልስ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ጥሩ ይዘት የነበረውን እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም የአቃቂ በሒደት መዳከም ግን ለመከላከያ አጥቂዎች ምቹነት የፈጠረላቸው ነበር፡፡ በተለይ ከአምና በተላለፈ ቅጣት ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች መሰለፍ ያልቻለችው መዲና አወል በተደጋጋሚ የአቃቂን የተከላካይ ክፍል በመረበሽ በርካታ ዕድሎችን አግኝታ በጠረቻቸው ቸልተኝነቷ አልተጠቀመቻቸውም። በተመሳሳይ ሴናፍ ዋቁማ ግልፅ የሆኑ ዕድሎችን ወደ ግብነት መለወጥ ሲቸግራት አይተናል፡፡
68ኛው ደቂቃ ላይ በመከላከል ዝንጉነትን በመጨረሻው ደቂቃ ሲያሳዩ የነበሩት አቃቂዎች ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል፡፡ በጥሩ የመቀባባል ሂደት የተገኘን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ሰጥታት መዲና ዐወል ከብዙ ሙከራዎች በኃላ ግብ አግብታ የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጋለች፡፡ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በግራ በኩል ተሰልፋ በነበረችው መሳይ ተመስገን ማራኪ ተሻጋሪ ኳሶች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ማጥቃት ላይ ትኩረት ሲያደርጉ የነበሩት መከላከያዎች 2 ለ 0 በማሸነፍ ተከታታይ ሁለተኛ ድላቸውን አሳክተዋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የመከላከያዋን የመስመር ተጫዋች መሳይ ተመስገንን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ