በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሦስተኛ ደረጃ ይዞ የተመለሰው ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ላይ ስለነበረው ቆይታ አሰልጣኙ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ወሎ ሠፈር በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ከተባለበት ሰዓት ዘግይቶ በጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እንድሪያስ በመግቢያ ንግግራቸው ይህን ብለዋል።
” ፌዴሬሽኑ ይህን ቦታ ከሰጠኝ ቀን ጀምሮ የተጫዋቾች ምልመላ አከናውኛለሁ። በምርጫው ወቅት ጊዜው የኮቪድ በመሆኑ ምርጫውን አክብዶብናል። ይህም ቢሆን ከተለያዩ የስፖርት ማዘወተሪያዎች፣ ፕሮጀክቶች፣ ክልሎች ከላኳቸው ሦስት ሦስት ተጫዋቾች፣ ከክለቦች እና አካዳሚዎች ለመጥራት ተሞክሯል። በዚህ ብሔራዊ ቡድን ምልመላ ወቅት ከ800 በላይ ታዳጊዎችን ለማየት ሞክረናል። ምርጫውን ስራችንን በጣም ያከበደው። ያም ሆኖ ስራችንን ለመወጣት ሞክረናል። ከዛም በኋላ የተመረጡትን ልጆች አዲስ አበባ እና ካፍ አካዳሚ በማስገባት ትንሽ ከባድ ልምምድ ሰጥተናል። ቅድም እንዳልኩት በወቅቱ ባመጣው ችግር ምክንያት ስልጠናውም ላይ ተፅዕኖ ነበረው። እንዲሁም እኛ የቸገረን ነገር ቢኖር ሌላው MRI ምርመራ ነበር።
ሆኖም ሁሉን ያሳበጠረ ቡድን ይዘን ወደ ሩዋንዳ አቅንተናል። ጨዋታው የነበረው ዋናው ከተማ ላይ ሳይሆን ከኪጋሊ የሶስት ስዓት መንገድ ተጉዘን ነበር።
” የመጀመሪያው ጨዋታ እድል ሆኖ እኛ ላይ ደርሷል። ተጫዋቾቼም ሆነ እኛ ብዙ ጥረናል። ልጆቹ የተቻላቸውን ሁላ መስዋዕትነት ከፍለው በመጀመሪያው ጨዋታ ከኬንያ ቡድን ጋር 2-2 በሆነ ውጤት ተለያይተናል። ተጋጣሚያችን ኬንያ ለብዙ ጊዜ አብረው መቆየት የቻሉ ነበሩ። ሆኖም በተጫዋቾቼ ጥረት አቻ ሆነናል።
ሁለተኛ ጨዋታችን የነበረው ከዩጋንዳ ጋር ነበር። ቡድኑ ውስጥ የእድሜ ጉዳይ በግልፅ የሚታይ ነው። አወዳዳሪው አካል ይህን ቢመለከትበት ጥሩ ነበር ባይ ነኝ፤ እዛም ይሄን ነው የተናገርኩት። ከዛም በኋላ በግማሽ ፍፃሜ ከታንዛንያ ቡድን ጋር ነበር የደረሰን። በእግር ኳስ አንዱ ቡድን ማሸነፍ ሌላው መሸነፍ ግዴታ የሆነበት ቦታ ስለነበር መደበኛውን ደቂቃ በአቻ ውጤት ተለያይተን በመለያ ምት ተሸንፈናል። ውጤቱ መጥቶ ቢሆን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያሳልፈን ነበር። ልጆቹ ታዳጊዎች ናቸው፤ ጥሩ ተሞክሮ ሆኖ አልፏል።
“በስተመጨረሻ የደረጃ ጨዎታ ለማድረግ የጁቡቲን ቡድን ነበር የገጥምነው። ተጋጣሚያችን ለጫውታው ትኩረት በማድረግ ዝግጅቱን ፈረንሳይ ነበር ሲያደርግ የነበረው። ነገር ግን ልጆቻችን ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር የጁቡቲን ቡድን በማሸነፍ የነሐስ ተሸላሚ ሆነዎል።”
በመቀጠል በዕለቱ በቦታው ከተገኙ ጋዜጠኞች ቡድኑ በሩዋንዳ ቆይታው ያላሳካው እቅድ ምንድነው? በቀጣይ የቡድኑ ቀጣይነት ላይ ምን ታቅዷል? የሚሉ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው የተነሱ ጥያቄዎችን አሰልጣኙ በተከታይ መልኩ ምላሽ ሰጥተዋል።
” የአፍሪካ ዋንጫ መግባት እንችል ነበር። ተጫዋቾቹም የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። በእውነት ሊመሰገኑ ይገባል። የእድል ጉዳይ ሆኖ በመለያ ምት ነው የተሸነፍነው”
“ቀጣይ እቅዴ፤ የአንድ ዓመት ኮንትራት አለኝ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተነጋግረናል። የተለያዩ ግኑኝነቶች እያደረግን ነው። ቴክኒካል ዳሬክተሩም እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ፌዴሬሽኑ እቅድ እንዳቀርብ አዞኛል። እሱ ላይ እየሰራሁ ነው። ልጆቹ በቀጣይ ተሰባስበው የሚሰሩበት ሁኔታ ይፈጠራል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ